ፑቲን የዩክሬን ወደቦችን ለእህል ጭነት ክፍት እንዲያደርጉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠየቀ
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ዩክሬን ብቻዋን 4 መቶ ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለመመገብ የሚያስችል አቅም አላት
ይህ ካልሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ርሃብ ይጋለጣሉ ሲሉ የፕሮግራሙ ዋና ዳይሬክተር ተማጽነዋል
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ወደቦችን ለእህል ጭነት ክፍት እንዲያደርጉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠየቀ፡፡
ፕሮግራሙ ወደቦቹ ካልተከፈቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ርሃብ ሊጋለጡ ይላሉ ብሏል፡፡
ይህን አለመፍቀድ በዓለም የምግብ ዋስትና ላይ "የታወጀ ጦርነት" ተደርጎ ይወሰዳልም ብሏል ፕሮግራሙ፡፡
ጉዳዩ ብዙዎችን ለርሃብ ከመዳረግም በላይ አለመረጋጋቶችን ሊያስከትልና የህገ ወጥ ስደተኞን ቁጥር ሊያንር እንደሚችል የፕሮግራሙ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሌይ ተናግረዋል፡፡
ቢዝሌይ ይህ ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን የርሃብ አደጋ የተጋረጠባቸውን ሌሎችንም ሃገራት እንደሚመለከት ነው የተናገሩት፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ትናንት ረቡዕ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ችግሩን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
"ፑቲን እባክዎትን የሚራራ ልብ ካለዎት ወደቦቹን ይክፈቱና ደሃዎችን እንመግብ አስከፊውን ርሃብም እናስቁመው" ሲሉም ተማጽነዋል ቢዝሌይ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ዩክሬን ብቻዋን 4 መቶ ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለመመገብ የሚያስችል አቅም አላት፡፡
ቢዝሌይ ኦዴሳ በተባለው የዩክሬን አካባቢ የሚገኙ ወደቦች ካልተከፈቱ ዩክሬን እንደ ሃገር የተቀረው ዓለምም ጭምር አደገኛ የግብርና ቀውስ እንደሚገጥመው ከሰሞኑ ጽፈው ነበር፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ራሳቸው ጦርነቱ ምን ያህል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከከፋ የርሃብ አፋፍ ላይ እንዳደረሰ ትናንት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ስንዴን መሰል የግብርና ምርቶች በተለያዩ አማራጮች ከዩክሬን ወጥተው ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት መድረስ የሚችሉበትን መንገድ ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር በመሆን እያፈላለገች መሆኗን አስታውቃለች፡፡