አንድ ጤነኛ ሰው ያለ ምግብ ስንት ቀን በህይወት መቆየት ይችላል?
በደላንታ ወረዳ ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ 20 ወጣቶች ዋሻ ውስጥ ከተቀበሩ 10ኛ ቀናቸው ይዘዋል
በወረዳው ከሶስት ዓመት በፊት 10 ወጣቶች ተመሳሳይ አደጋ ደርሶባቸው ከ11 ቀናት በኋላ በህይወት የተገኙት አራቱ ብቻ ነበሩ
አንድ ጤነኛ ሰው ያለ ምግብ ስንት ቀን በህይወት መቆየት ይችላል?
ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ 018 ቀበሌ ልዩ ስሙ አለኋት ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነበር ኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ወጣቶች መውጫ ስፍራ በአለት የተደፈነባቸው፡፡
ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው በማህበር ተደራጅተው ኦፓል በማውጣት ላይ የነበሩ እነዚህ ወጣቶች ቁጥራቸው 20 ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ የወጣቶቹን ህይወት ለመታደግ ሌት ተቀን እየቆፈረ ነበር።
የደላንታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት የወጣቶቹን ህይወት ለመታደግ የወረዳው እና የአካባቢው ማህበረሰብ ሌት ተቀን በፈረቃ እየቆፈረ እንደነበር ነገር ግን መልክዓ ምድሩ ለቁፋሮ አመቺ አለመሆኑን ተከትሎ ተጨማሪ ሰው ላለማጣት በሚል እና ጉዳዩ ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ ቁፋሮው እንዲቆም ተደርጎ ነበር ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት ፣ የክልሉ መንግሥት እና የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳድር ለደላንታ ወረዳ ባደረገው የባለሙያ እና ቁሳቁስ ድጋፍ አማካኝነት ወጣቶቹን ለመታደግ ዳግም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
እነዚህ ወጣቶች መውጫቸው ተደርምሶባቸው መሬት ውስጥ ከሆኑ ዛሬ 10ኛ ቀናቸው ላይ ሲሆኑ አንድ ሰው ምን ያህል ያለ ምግብ መቆየት ይችላል በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ባለሙያ አነጋግረናል።
ዶክተር ነጋ ናማጋ የምግብ ሳይንስ ባለሙያ ሲሆኑ አንድ ሰው ምን ለያህል ጊዜ ያለ ምግብ በህይወት ሊቆይ ይችላል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን መልሰውልናል።
"አንድ ጤነኛ ሰው ውሀን ጨምሮ ያለ ምግብ እስከ አንድ ወር በህይወት ሊቆይ ይችላል ፣ ነገር ግን በአደጋ፣ ፍርሀት እና ጭንቀት ውስጥ ከሆኑ ግን በህይወት የሚቆዩበት ጊዜ ከዚህ ሊያጥር ይችላል" ብለዋል።
"እንደ ዳላንታው አይነት አደጋ ያጋጠማቸው ሰዎች በህይወት መቆየት አለመቆየታቸው የሚወሰነው እያንዳንዳቸው ያላቸው የሰውነት ሁኔታ፣ ተጓዳኝ ህመም፣ በሰውነታቸው ውስጥ ያላቸው ውሀ መጠን እንዲሁም በሽታ የመከላከል አቅም በህይወት የሚቆዩበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል " ሲሉም ባለሙያው ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ላይ ማዕድኑን ለማውጣት እየቆፈሩ እያሉ መውጫቸው በዓለት የተዘጋባቸው ሲሆን በአካባቢው በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ጉዳዩን ለህዝብ አሳውቀዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በዚሁ ወረዳ በተመሳሳይ ኦፓል ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ የነበሩ 10 ወጣቶች ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሟቸው አራቱ ብቻ በህይወት መገኘት ችለው እንደነበር ተገልጿል።