“ኡጋንዳ የንግድ ግንኙነት የሚኖራት ከሚያከብሯት ሀገራት ጋር ብቻ ነው” - ሙሴቬኒ
ፕሬዝዳንቱ የምዕራባውያን ጫናዎች በካምፓላ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ተጽዕኖ አለመፍጠራቸውንም ተናግረዋል
ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከላክል ህግ ማውጣቷ በምዕራባውያን ተቃውሞና ጫና አስከትሎባታል
ኡጋንዳ በምዕራባውያን ጫና ምክንያት ምጣኔ ሃብቷ ምንም ተጽዕኖ እንዳልደረሰበት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተናገሩ።
በአወዛጋቢና ምዕራባውያንን በሚወርፍ ንግግራቸው የሚታወቁት ሙሴቬኒ በብሄራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ፥ “የምዕራባውያን ጫና ምንም ትርጉም የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ሀገራቸው ጠባቂ ሳትሆን “ሀብት ፈጣሪ ሀገር” መሆኗን ነው።
ኡጋንዳ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክልና እስከ ሞት የሚያስቀጣ ህግ ማውጣቷ በምዕራባውያን ከፍተኛ ውግዘት ገጥሞታል።
የአለም ባንክ ለሀገሪቱ ብድር ከመከልከሉ ባሻገር አሜሪካም ካምፓላን ለአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው የቀረጥ ነጻ እድል (አጎዋ) ማስወጣቷ የሚታወስ ነው።
የባንኩንም ሆነ የዋሽንግተንን ጫና በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ እንደሆነ ያነሱት ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ፥ “የኢምፔሪያሊስቶች ከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂን ቀድመን ስለተረዳን ጊዜያቸውን ባያጠፉ ይሻላቸዋል” ማለታቸውንም ቢዝነስ ኢንሳይደር አስነብቧል።
ከምዕራባውያን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ለመላቀቅ ኡጋንዳውያን የሀገር ፍቅርና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።
ካምፓላ ቀጠናዊ ውህደትን ለማጠናከር እንደምትሰራ ያብራሩት ሙሴቬኒ፥ “ይህን ካላደረጋችሁ ይህን አንፈቅድላችሁም ከሚሉን ጋር ሳይሆን ከሚያከብሩን ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነታችን እናጠናክራለን” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ተንታኞች ግን ከአሜሪካ ለጤና እና ሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ድጋፍ ታገኝ የነበረችው ኡጋንዳ በዋሽንግተን የአጎዋ ማዕቀብ ምንም ጉዳት አላስተናገደችም የሚለው የሙሴቬኒ ንግግር ብዙም አሳማኝ አይመስልም ይላሉ።
ካምፓላ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ማገዷ ውግዘትና ጫና ቢያበዛባትም የሙሴቬኒ አስተዳደር እስከሞት የሚያስቀጣውን ህግ ለመሻር አልፈቀደም።