አሜሪካ በኡጋንዳ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው በሚል ከአግዋ እድል መሰረዟ ይታወሳል
አሜሪካ ለራሷ የተጋነነ ግምት እንዳላት የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ተናገሩ፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባሳለፍነው ሳምንት ምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳን ጨምሮ አራት ሀገራትን ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አግዋ) እድል መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ኡጋንዳን ከዚህ እድል ያገደችው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው በሚል ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮሪ ካጉታ ሙሴቪኒ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በምላሻቸው አሜሪካ ለራሷ ያላት ግምት የተጋነነ ነው፣ አፍሪካ ያለ እነሱ እርዳታ የሚኖሩም አይመስላቸውም ብለዋል፡፡
ኡጋንዳ የራሷን እድገት እና ልማት በራሷ ማሳካት እንደምትችል ታምናለች ያሉት ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ያለ ምዕራባዊያን እርዳታ መኖርም እንችላለን ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክል እና እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ ህግ ባሳለፍነው ግንቦት ላይ ማጽደቋ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የኡጋንዳ መንግስትን የወቀሱ ሲሆን የዓለም ባንክ ብድር እንደማይሰጥ አስታውቆም ነበር፡፡
ኡጋንዳ ያለዓለም ባንክ ድጋፍ ህይወትን ለመቀጠል ማቀዷ ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒም የዓለም ባንክ ምን ማድረግ እንዳለብን ሊያስገድደን ይፈልጋል ኡጋንዳ ያለ ዓለም ባንክ ብድር ማደግ ትችላለች ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አሜሪካ ለኡጋንዳ በተለይም ለጤና ስራዎች ከፍተኛ በጀት ከሚያፈሱ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን የጸረ ኤችአይቪ ኤድስ መድሃኒት ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምታደርግ የምትጠበቀው ኡጋንዳ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ይወዳደሩ አይወዳደሩ እስካሁን አልተገለጸም፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ አነጋጋሪ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቀው ልጃቸው ሙሁዚ ኬንሩጋባ ሙሴቪኒ በምርጫው አባቱን ወክሎ ሊወዳደር እንደሚችል ተጠብቋል፡፡