ሙሴቬኒ በጠንካራ ስራ እንጂ የመንግስትን ንብረት በመዝረፍ ያከማቸሁት ሃብት የለም አሉ
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ከልጃቸው ጋር የተነሱት ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል
ስልጣን ከያዙ 31 አመት የሆናቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሰፊ የእርሻ መሬት አላቸው
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ያካበቱት ሃብት በጠንካራ ስራ እና የግል ቢዝነስ እንጂ ከመንግስት በመመዝበር የተገኘ እንዳልሆነ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ይተካቸዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ልጃቸው ጀነራል ሙሆዚ ካይነሩጋባ እና ባለቤታቸው ጋር የተነሱት ምስል በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።
ሙሴቬኒ በትውልድ መንደራቸው ኑቱንጋሞ እና ዋኪቱራ በተባለ አካባቢ ሰፊ የእርሻ ማሳ አላቸው፤ የከብት ማድለቢያዎቻቸውም ስጋ እና ወተት በስፋት የሚያቀርቡ ናቸው ተብሏል።
ከሰሞኑም በአንደኛው የእርሻ ማሳቸው ውስጥ በተዘጋጀ ድግስ ላይ የተነሱትና ያጋሩት ምስል የሃብት ምንጫቸውን ዳግም ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጓል።
ላለፉት 31 አመታት ኡጋንዳን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ግን ባለፉት አራት አስርት አመታት ያካበትኩት ሃብት በጠንካራ ስራ እና የግል ጥረት እንጂ ከመንግስት በመመዝበት የተገኘ አይደለም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከፈረንጆቹ 1965 በፊት አንድም የቤተሰባቸው አካል የመንግስት ስራ ላይ እንዳልነበረ አውስተዋል።
እሳቸውም የመጀመሪያ ስራቸው መምህርነት እንደነበርና ከ63 አመት በፊት ትግል ከጀመሩ በኋላም መጠነኛ ጥቅም ያግኙ እንጂ በግላቸው ሃብት እንዳልፈጠሩም ነው የተናገሩት።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የሙሴቬኒ ሃብት 4 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይገምታሉ፤ አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር በዘገባው አሃዝ ባያስቀምጥም ፕሬዝዳንቱ የግብርና ምርቶችን በመሸጥ ሃብት ማከማቸታቸውን አብራርቷል።
“የኡጋንዳ የምግብ ሃብት ያኮራኛል፤ ካሳቫ፣ በቆሎ፣ ስጋ፣ ወተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት አለን፤ በርካታ የአውሮፓ ሃገራት በምግብ እጦት ሲያለቅሱ እኛ ጋር ሁሉም ነገር አለ” ያሉት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፥ በዚህ ሃብት ላይ ቴክኖሎጂን እሴት ጨምረው ሃብት እንደፈጠሩ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በትግል ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች “ከብቶች ተዘርፈው ተበልተዋል፤ እስካሁን ለባለቤቶቹ ካሳ አልተከፈላቸውም” የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸዋል።
“የኡጋንዳ ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር በቡጋንዳ ለባለቤቶቹ ክፍያ ፈጽሞ ከብቶችን አርዶ በልቷል፤ በበርካታ አካባቢዎች ከብቶችን ዘርፎ የበላው የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ ነው” ሲሉም የሚመሩት መንግስት ካሳ መክፈሉን አብራርተዋል።
የቀድሞው ታጋይ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ስለአምባገነን መሪነታቸው ሲጠየቁም “አምባገነን ስርአት ከተባለም የኡጋንዳ ከብሪታንያ ይሻላል፤ ጊዜውን የጠበቀና ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች በፓርላማ እና በወረዳ ምክርቤቶች የሚወከሉበት ምርጫ እናደርጋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።