በኡጋንዳ ግብረሰዶም ፈጽሟል የተባለው ወጣት የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተነገረ
የ20 አመቱ ወጣት በአዲሱ የሀገሪቱ የጸረ ግብረሰዶም ህግ በሞት ሊቀጣ የሚችል የመጀመሪያው ግለሰብ ይሆናል
ኡጋንዳ በግንቦት ወር ያጸደቀችው ህግ የአለም ባንክ ብድርን አስከልክሏታል
ኡጋንዳ ግብረሰዶማዊ ነው ያለችውን ወጣት በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ተነገረ።
የ20 አመቱ ወጣት በተከሰሰበት የግብረሰዶም መፈጸም ወንጀል ከሁለት ሳምንት በፊት ፍርድ ቤት መቅረቡ ተነግሯል።
በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ሶሮቲ በተባለች ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበው ተከሳሽ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን እስኪመለከት እየጠባበቀ ነው ተብሏል።
- ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ “የዓለም ባንክ ባህላችንን እና ሀይማኖታችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው” አሉ
- "እየሱስን ለማግኘት" ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 80 ኡጋንዳዊያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
ኡጋንዳ ከፈረንጆቹ 2005 ወዲህ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ አላደረገችም፤ ይሁን እንጂ የሞት ቅጣት ውሳኔ ማሳለፍን አልከለከለችም።
ካምፓላ በግንቦት ወር ያወጣቸውና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከለክለው ጠበቅ ያለ የጸረ ግብረሰዶም ህግ የሞት ቅጣትን የሚያስከትሉ ወንጀሎችን ዘርዝሯል።
አዲሱ ህግ በማንኛውም የግብረሰዶማዊነት ተግባር የተሳተፈ አካል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ያዛል።
ወንጀሉ የተፈጭጸመው በህጻናት እና በአቅመ ደካሞች ላይ ከሆነ ደግሞ በሞት እንደሚያስቀጣ ነው የሚያስቀምጠው።
በዚህም ምክንያት የአለም ባንክ በቅርቡ ለኡጋንዳ ብድር መከልከሉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒም “የዓለም ባንክ ባህላችንን እና ሀይማኖታችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው" በማለት የባንኩን ውሳኔ መቃወማቸው አይዘነጋም።
ኡጋንዳ ያለ ዓለም ባንክ ብድር ማደግ እንደምትችልም ነው ሲናገሩ የተደመጡት።