የቀድሞ ፕሬዘዳንት ሀብሬ በሴኔጋል በእስር ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል
የቀድሞው የቻድ ፕሬዘዳንት በ79 ዓመታቸው በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው አለፈ።የቀድሞው የቻድ ፕሬዘዳንት በሴኔጋል በእስር ላይ እያሉ ህይወታቸው ማለፉን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ቻድን ከፈረንጆቹ 1982 አስከ 1990 ዓመት ድረስ በፕሬዘዳንትነት የመሩት ሂሴን ሀብሬ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ፈጽመውታል በተባሉበት የሰብአዊ መብት ጥሰት በእስር ላይ ነበሩ።
ፕሬዘዳንቱ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ስምነት ዓመታት ውስጥ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን በመግደል እና ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንደፈናቀሉ አድርገዋል የሚሉ ክሶች ቀርቦባቸዋል።
ሂሴን ሀብሬ በቀረበባቸው ክስ ምክንያትም በአፍሪካ ህብረት በሚደገፈው የሰብአዊ መብት ወንጀል ችሎት በፈረንጆቹ 2016 ከሚኖሩበት ፈረንሳይ ተይዘው ወደ ሴኔጋል በመምጣት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።
የፍርድ ጊዜያቸውን በመፈጸም ላይ እያሉ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በ79 ዓመታቸው ህይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።
አሜሪካ የቀድሞ የሊቢያ ፕሬዘዳንት የነበሩትን ሞአመር ጋዳፊን ለመውጋት በሚል በአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ እና በፈረንሳይ ድጋፍ ወደ ስልጣን እንደመጡ የሚነገርላቸው እኝህ ግለሰብ በፈረንጆቹ 1990 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን እንደተነሱ ዘገባው አክሏል።