ቁማር፣ የመጠጥ ሱስ እና የትዳር ፍቺ ተጫዋቾቹን ለድህነት የዳረጉ ምክንያቶች ናቸው
ባንድ ወቅት ሀብታም የነበሩ እና አሁን በድህነት ውስጥ ያሉ እግር ኳስ ተጫዋቾች
የእግር ኳስ ተጫዋቾች በዓለማችን ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙ ስፖርተኞች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ብዙዎቹ ኮኮብ ተጫዋቾች ለአጭር ጊዜ ጥሩ ክፍያዎችን የሚያገኙ ቢሆንም ገንዘባቸውን ከብክነት በማዳን ወደ ዘላቂ ኢንቨስትመንት በመቀየርም ይታወቃሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ባንድ ወቅት በአውሮፓ ተወዳጅ ሊጎች ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ እና ጥሩ ክፍያ ሲያገኙ የነበሩ ጥቂት የቀድሞ ተጫዋቾች በድህነት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል፡፡
በሊቨርፑል፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ክለቦች ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ የተወሰኑ የቀድሞ ኮኮቦች አሁን ህይወታቸው በድህነት ውስጥ መሆኑን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
ዌስ ብራውን፣ኢምሊ ሄስኪ፣ቻርሊ ቴይለር፣ ጄምስ፣ፖል ጋስኮኝ፣ ጀርሚ ፔናንት፣ሬሲ እና ሌሎችም በድህነት ውስጥ እየኖሩ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር ከነበሩ ተጫዋቾ መካከል አንዱ የነበረው ዌስ ብራውን በሳምንት 50 ሺህ የሮ ይከፈለው የነበረው ሲሆን በክለቡ ውስጥ ከነበሩ ኮኮብ ተጫዋቾ ጋር ፉክክር በመግባት በየሳምንት ገንዘቡን ሲያባክ ነበር ተብሏል፡፡
ይሁንና እድሜው እየጨመረ ሲመጣ እና ክፍያው እየቀነሰ ሲሄድ በመጠጥ ሱስ ከመውደቁ ባለፈ ያለውን ገንዘብ ባለመቆጠቡ ምክንያት ለመሰረታዊ ፍጆታዎች የሚያወጣው ገንዘብ እስከ ማጣት መድረሱ ተገልጿል፡፡
ሌላኛው በድህነት ውስጥ እየኖረ ነው የተባለው ተጫዋች ከሊቨርፑል ጋር የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ጆን ሪሴ አንዱ ነው፡፡
ይህ ተጫዋች የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ባነሳ በሁለት ዓመት ውስጥ በቁማር ምክንያት ገንዘቡን አጥቷል የተባለ ሲሆን ህይወቱን በድህነት ለመምራት ተገዷል፡፡
ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎችን ተሰልፎ መጫወት የቻለው ፖል ጋስኮኝ 20 ሚሊዮን ዩሮ ሀብት የነበረው ቢሆንም አደገኛ ዕጾችን በመጠቀም፣ በመጠጥ እና ሌሎች ሱሶች ምክንያት ገንዘቡን ካጣ በኋላ ህይወቱን በድብርት እና ጭንቀት እያሳለፈ ነው ተብሏል፡፡
የቀድሞ ቶትንሃም ሆትስፐር፣ ሬንጀርስ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ጋስኮኝ በግብር ስወራ እና ሌሎች ክሶችም ክስ ተመስርቶበት ነበር፡፡
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ የሊቨርፑል፣ ማንችስተር ሲቲ እና ሌሎችም ክለቦች ግብ ጠባቂ የነበረው ዴቪድ ጀምስ በቁማር ምክንት የነበረውን ገንዘብ ማጣቱ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ከትዳር አጋሩ ጋር የነበረውን ልዩነት መፍታት ባለመቻሉ ትዳሩ የፈረሰ ሲሆን ቀሪ ሀብቱን ለማካፈል ተገዷል፡፡
ሌላኛው የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ጀርሜን ፔናንት ያለውን ገንዘብ በመጠጥ ምክንያት ማጣቱን ተከትሎ ቀሪ ህይወቱን በእዳ እና ድህነት እያሳለፈ ነው ተብሏል፡፡