የ9 አመት እስር የተፈረደበት ብራዚላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሮቢኒሆ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ
በአስገድዶ መድፈር ክስ ላለፉት 6 ወራት በእስር ቤት የሚገኘው ሮቢኒሆ የእስር ጊዜው እንዲቀነስለት ነበር ይግባኝ የጠየቀው
የተጫዋቹ ጠበቆች በቀጣይ ይግባኛቸውን ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል
የ9 አመት እስር የተፈረደበት ብራዚላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሮቢኒሆ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ።
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና ማንችስተር ሲቲ እግርኳስ ተጫዋች ብራዚላዊው ሮቢኒሆ የእስር ጊዜው እንዲቀነስለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተጫዋቹ በጣሊያን በሚገኝ መሸታ ቤት ውስጥ በአልባኒያዊት ሴት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ክስ የቀረበበት በ2013 ነበር፡፡
በዚህ ጥቃት ተሳትፈዋል ከተባሉ ስድስት ሰዎች መካከል ሮቢኒሆ እንደኛው ሲሆን በተጫዋቹ ላይ አለማቀፋዊ የእስር ማዘዣ ወጥቶበት የነበረ ቢሆንም በብራዚል ሳኦፖሎ ተደብቆ ቆይቷል፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ የ9 አመት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ላለፉት 6 ወራት ብራዚል በሚግኝ እስር ቤት ስምንት በሁለት በሆነ አነስተኛ ክፍል ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል፡፡
የ60 ሚሊየን ዩሮ ሀብት ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለት ሮቢኒሆ ጠበቆች የተጫዋቹ የክስ መዝገብ እንዲሻሻል እንዲሁም የተወሰነው ቅጣት በገንዘብ እንዲቀየርለት እና የእስር ጊዜው እንዲቀንስ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ተደርጓል፡፡
በተደጋጋሚ ድርጊቱን እንዳልፈጸመ ሲናገር የሚደመጠው ተጫዋቹ ክሱ በጣሊያን የተስፋፋው ዘረኝነት መገለጫ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
ከሳለፍነው ሀምሌ ጀምሮ የደንበኛቸውን የእስር ጊዜ ለማስቀነስ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ጠበቆች ጉዳዩን ወደ ሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት እና ይግባኛቸውን በድጋሚ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
ሮቢኒሆ ባለፉት 6 ወራት ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጥገናን በመሰልጠን በእስርቤቱ የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በመጠገን እንዲሁም ከታሳሪዎች ጋር እግር ኳስ በመጫወት ጊዜውን እንደሚያሳልፍ ዘ ሰን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኝበት እስር ቤት “የምድር ሲኦል” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ነፍሰ ገዳዮች እና አስገድዶ ደፋሪዎችን ጨምሮ ከባባድ ወንጀለኞች የሚታሰሩበት በመሆኑ ጠበቆቹ ለተጫዋቹ ስነልቦናዊ ጤንነት እንደሚሰጉ ተናግረዋል፡፡
ለሪያል ማድሪድ ፣ ለኤሲ ሚላን እና ማንችስተር ሲቲ ክለቦች በመጫወት ዝናን ያተረፈው ብራዚላዊ በ2020 ወደ ቀድሞ ክለቡ ሳንቶስ ተመልሶ በመጫወት ላይ ነበር፡፡