ኃላፊው ጥሪ ያቀረበው እስራኤል በሀማስ የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ የምትሰጠውን የአጸፋ ምላሽ በማጠናከሯ ምክንያት ነው
የቀድሞው የሀማስ ኃላፊ ካሊድ ማሻል ጎረቤት ሀገራት እየተደረገ ባለው የጸረ- እስራኤል ውጊያ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኃላፊው በመጭው አርብ እለት በሙስሊሙ አለም ሰልፍ እንዲደረግ እና የጎረቤት ሀገራት ህዝቦች እየተካሄደ ባለው የጸረ- እስራኤል ውጊያ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
"በአረብ እና በሙስሊሙ አለም ወደሚገኙ አደባባዮች እና መንገዶች እናመራለን" ሲሉ በአሁኑ ወቅት የሀማስን የዲያስፖራ ቢሮ የሚመሩት ማሻል ተናግረዋል።
መቀመጫውን ኳታር ያደረገው ማሻል የጆርዳን፣የሶሪያ፣ የሊባኖስ እና የግብጽ ህዝብና መንግስታት ፍልስጤማውያንን የመርዳት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ማሻል"የጆርዳን ጎሳዎች፣ የጆርዳን ልጆች፣ ወንድሞች እና እህቶች... ድንበሩ ቅርባችሁ ነው። ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ታውቃለችሁ" ብሏል።
ጆርዳን እና ሊባኖስ ከፍተኛ የፍልስጤም ስደተኞች ያሉባቸው ሀገራት ናቸው።
ማሻል ይህን ጥሪ ያቀረበው እስራኤል በሀማስ የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ የምትሰጠውን የአጸፋ ምላሽ በማጠናከሯ ምክንያት ነው።
እስራኤል በአንድ ሌሊት በጋዛ የሚገኙ 200 ኢላማዎች መትታለች።
ሀማስ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን ጥቃት ባለፈው ቅዳሜ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ማድረስ ችሏል።
"ሁላችሁም ጂሃድ የምትማሩ እና የምታስተምራ አዋቂዎች ይህ በተግባር የምንገለጥበት ጊዜ ነው" ሲልም ማሻል ጥሪ አስተላልፏል።
እስራኤል የሀማስ መቀመጫ የሆነችውን ጋዛን ከበባ ውስጥ በማስገባት ማጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።