በእስራኤል ላይ ጥቃት ያቀነባበረው ሚስጥራዊው የሀማስ አዛዥ ማን ነው?
እስራኤል በ50 አመታት ውስጥ አይታው የማታውቀውን ጥቃት ያቀናበረው የሀማስ አዛዥ በግልጽ አይታወቅም
"እንግዳ" ወይም አንዳንድ ጊዜ "ዘጠኝ ነፍስ ያላት ድመት" እየተባለ የሚጠራው ዲይፍ የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ነው
ሀማስ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት በ50 አመታት ውስጥ ከባድ የተባለ ጥቃት አድርሷል።
ጥቃቱን ከጀርባ ሆኖ አቀናብሯል የተባለው አዛዥ ሞሀመድ ዲይፍ ይባላል።
"እንግዳ" ወይም አንዳንድ ጊዜ "ዘጠኝ ነፍስ ያላት ድመት" እየተባለ የሚጠራው ዲይፍ የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ነው። ዲይፍ ማለት በአረብኛ እንግዳ ማለት ሲሆን ይህን ሰም ያወጡለት እናቱ ናቸው።
ዲይፍ እንዳይታወቅ የተለያየ ባህሪይ በመላበሱ ምክንያት ነበር እናቱ "እንግዳ" ብለው ስም ያወጡለት።
ሁለተኛው መጠሪያው የተሰጠው ከእስራኤል ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች ያመለጠበትን ሁኔታ ለማመልከት ነው።
ዲይፍ በጣም አልፎ አልፎ መግለጫ ይሰጣል።
ሀማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ካደረሰ ከሰአታት በኋላ ዲይፍ ሪከርድ በተደረገ ድምጽ "ኦፐሬሽን አል አስቃ ስቶርም" መጀመሩን አስታውቋል።
"ይበቃናል" ያለው ዲይፍ ፍልስጤማውን ውጊያውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።
አዛዡ እንደገለጸው ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት ጥቃት የሰነዘረው 16 አመታት ለቆየው የጋዛ ከበባ፣ ለዌስትባንክ ወረራ እና በአል አስቃ ለደረሰው ጥቃት አጸፋዊ መልስ ለመስጠት ነው ብሏል።
"እነዚህ ሁሉ(ችግሮች) እንዲቆሙ ወስነናል" ሲልም ተደምጧል ዲይፍ።
የማይታየው ወታደራዊ አዛዥ
ዲይፍ ሀማስን በፈረንጆቹ በ1990 በመቀላቀል ታዊቂ ቦምብ ሰሪ ከሆነው ኢንጂነር ያሃያ አያሽ ቦምብ መስራትን ተምሯል።
በፈረንጆቹ ከ1995 ጀምሮ አጥፍቶ ጠፊዎችን በማስታጠቅ በደርዘን ለሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሞት ተጠያቂ ነው የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ዲይፍ በጋዛ ሰርጥ የተሰራው ውስብስብ የመሬት ውስጥ ቱቦ እና የቃሳም ሮኬት መሀንዲሱ እሱ ነው ይባላል።
ዲይፍን ከ1990ዎቹ ጀምሮ የሚያውቀው የሀማስ ምንጭ ለሮይተርስ እንደገለጸው ዲይፍ ታጣቂ ቡድኑ ሲመሰረት ጀምሮ ሚና ነበረው።
ቀድሞ የቃሳም ብርጌድ መሪ በእስራኤል ከተገደለ በኋላ ዲይፍ በፈረንጆቹ 2002፤ የብርጌዱ መሪ መሆን ቻለ።
አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የሀማስ መሪ ኢማድ ፋሎጂ በፈረንጆቹ 2014 ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት ዲይፍ ብዙ አለመታወቁ ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል።
የዲይፍን ፎቶ ወይም መረጃ ከህዝብ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።
"ብዙ እንዳይታወቅ ተራ ሰው በመምሰል ከህዝብ ተቀላቅሎ ይኖራል። በተለያዩ ማንነቶች እና ፖስፖርቶች ይንቀሳቀሳል።" ይላሉ ኢማድ ፋሎጂ
ፋሎጂ ለጋዜጣው እንደገለጹት በእስራኤል ጉዳይ ያለው ጠንካራ አቋም የፍልስጤምን ህዝብ ፍላጎት በትክክል ያንጸባርቃል።
ዲይፍ ከ1995 ጀምሮ በእስራኤል በጥብቅ የሚፈለግ እና በርካታ የግድያ ሙከራዎችን ያለመለጠ ሰው ነው።
ነገርግን ከጉዳት አላመለጠም። በከፊል መንቀሳቀስ እንደማይችል እና ዊልቸር እንደሚጠቀም ይነገራል።
በእሱ ከላይ ከተሰነዘሩት በአንደኛው ጥቃት አንድ አይኑን እና እጁንም አጥቷል ይባላል። በፈረንጆቹ 2014 እስራኤል ዲይፍን ኢላማ አድርጋ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን አጥቷል።
እንደእስራኤል ሚዲያዎች ዘገባ የእስራኤል መንግስት ዲይፍን አሁንም ለመግደል እየፈለገው ነው።
ዲይፍ በአሜሪካ አለምአቀፍ አሸባሪ ዝርዝር ውስጥ ስሙ ተካቷል።
ዲይፍ በ1960ዎቹ በጋዛ በሚገኘው በካሀን ዮኒስ የስደተኞች ካምፕ ነው የተወለደው። ያደገበት ሁኔታ ብዙም አይታወቅም።