የ61 አመቱ ማጉፉሊ በልብ ህመም ምክንያት መሞታቸውን መንግስት አስታውቋል
ከሰሞኑ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳነት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ የቀብር ሥነ ስርዓት በቀጣዩ አርብ እንደሚካሄድ የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡
አዲሷ ፕሬዝዳንት የቀብር ስነስርዓቱ ሀሙስ እንደሚካሄድ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ ስነ ስርዓቱ ግን አርብ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ዕለቱ የተቀየረው ከዛንዚባር የሚመጡ ሰዎች፤ የጆን ማጉፉሊን አስክሬን መሰናበት እንዲችሉ መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በዚህም መሰረት ከዛንዚባር የሚመጡት ዜጎች ማክሰኞ አስክሬን የመሰናበት መርሃ ግብር የሚያደርጉ ሲሆን የዳሬሰላም፣ የሙዋንዛ እና የአዲሷ ዋና ከተማ ዶዶማ ነዋሪዎችም አስክሬ የመሰናበት መርሃ ግብር ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የ61 ዓመቱ ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ዳሬሰላም በሚገኝ ሆስፒታል ህይወታቸው ማለፉን መሪ ሆነው የተተኩት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ይፋ አድርገው ነበር፡፡ የህልፈታቸው ምክንያት ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ እንደሆነም ገልፀዋል።
ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን የ14 ቀናት ሀዘን እንደሚታወጅ እና በዚህ ጊዜ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ከሁለት ሳምንታት በላይ ለህዝብ አለመታየታቸውን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ስለመታመማቸው ጭምጭምታዎች በሰፊው ሲናፈሱ ነበር። ምንም እንኳን ባይረጋገጥም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በኮቪድ-19 ተይዘዋል ሲሉም ነበር።