ሳሚያ እስከ ጆን ማጉፉሊ ህልፈተ ህይወት ድረስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው
ሳሚያ ስሉሁ ሃሰን 6ኛዋ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡
ሳሚያ ህልፈተ ህይወታቸው የተሰማውን ጆን ማጉፉሊን ተክተው ነው በዳሬሰላም ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት።
ከደቂቃዎች በፊት ቃለ መሀላቸውን የፈጸሙት ፕሬዘዳንት ሳሚያ ታንዛኒያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት ይመራሉ ተብሏል፡፡
ይህም ላለፉት 7 ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩትን የ61 ዓመቷን አዛውንት ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር በ1960 በዛንዚባር ራስ ገዝ አስተዳደር የተወለዱት ሳሚያ ከ2015 ጀምሮ የማጉፉሊ ካቢኔ አባል ሆነው አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በህዝብ አስተዳደር 2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውም ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የታንዛኒያ ፓርላማ አባል እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ባለትዳር እና የ4 ልጆች እናትም ናቸው ሳሚያ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከህዝብ እይታ የመሰወራቸው ጉዳይ ሲያነጋግር የነበሩት ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ትናንት የማረፋቸው ዜና ተሰምቷል።
በፕሬዝዳንቱ ሞት ምክንያትም ታንዛኒያ 14 ብሔራዊ የሀዘን ቀናትን አውጃለች።
ጎረቤቷ ኬንያም የስድስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማወጇን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል። የኬንያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ዛሬ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ሊያደርግ የነበረውን የወዳጅነት ጨዋታ ለማጉፉሊ ክብር ሲባል መሰረዙንም የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
እንደ ታንዛኒያ ህገ መንግስት አንቀጽ 37 (2) ከሆነ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት በሞት አልያም በሌላ በማንኛውም ምክንያት በስልጣን ላይ ሆኖ አገሪቱን መምራት ካልቻለ ምክትል ፕሬዘዳንቱ እንዲመሩ ይፈቅዳል።