ሳሚያ ዛሬ ህልፈተ ህይወታቸው የተሰማውን ጆን ማጉፉሊን ተክተው ነው መሪነቱን የሚረከቡት
ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን ጆን ማጉፉሊን ተክተው ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት እንደሚመሩ ተገለጸ፡፡
በዓለ ሲመታቸው በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ተፈጽሞ ታንዛኒያን ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት በ6ኛ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚመሩ ይሆናሉም ተብሏል፡፡
ይህ ላለፉት 7 ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩትን የ61 ዓመቷን አዛውንት ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር በ1960 በዛንዚባር ራስ ገዝ አስተዳደር የተወለዱት ሳሚያ ከ2015 ጀምሮ የማጉፉሊ ካቢኔ አባል ሆነው አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በህዝብ አስተዳደር 2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውም ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የታንዛኒያ ፓርላማ አባል እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ባለትዳር እና የ4 ልጆች እናትም ናቸው ሳሚያ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከህዝብ እይታ የመሰወራቸው ጉዳይ ሲያነጋግር የነበሩት ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ ዛሬ የማረፋቸው ዜና ተሰምቷል።
በፕሬዝዳንቷ ሞት ምክንያትም ታንዛኒያ 14 ብሔራዊ የሀዘን ቀናትን አውጃለች።
ጎረቤቷ ኬንያም የስድስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማወጇን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል። የኬንያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ዛሬ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ሊያደርግ የነበረውን የወዳጅነት ጨዋታ ለማጉፉሊ ክብር ሲባል መሰረዙንም የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
እንደ ታንዛኒያ ህገ መንግስት አንቀጽ 37 (2) ከሆነ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት በሞት አልያም በሌላ በማንኛውም ምክንያት በስልጣን ላይ ሆኖ አገሪቱን መምራት ካልቻለ ምክትል ፕሬዘዳንቱ እንዲመሩ ይፈቅዳል።