የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 አመታቸው ህይወታቸው አለፈ
ካርተር በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ቀውስ በብዙ ቢፈተኑም በእስራኤል እና ግብጽ መካከል ሰላምን በመፍጠር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል

ከኋይት ሀውስ ከወጡ በኋላ ረጅም እድሜ ከኖሩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል ካርተር ቀዳሚው ናቸው
ኦቾሎኒ ገበሬነት እስከ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነት የዘለቁት ጂሚ ካርተር በ100 አመታቸው በጆርጂያ በሚገኝው መኖሪያቤታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡
ጄምስ ኤርል ካርተር ጁኒየር የተወለዱት በጥቅምት 1924 በጆርጂያ ውስጥ ሲሆን በ1946 ከአሜሪካ የባህር ኃይል አካዳሚ ተመርቀዋል ቀጥሎም በኒዩክሌር ሰርጓጅ መርሀ ግብር ውስጥ አገልግለዋል፡፡
በህይወቴ ትልቅ ዋጋ የምሰጠው ነገር ቤተሰብ ነው የሚሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ1946 ከባለቤታቸው ሮዛሊንን ጋር ትዳር መስርተው ሶስት ወንድና አንድ ሴት ልጅ ወልደዋል፡፡
ከ1971 እስከ 1975 በጆርጂያ ግዛት አስተዳዳሪነት ቆይተው በ1976 የዴሞክራቲክ ፕሬዝዳንታዊ እጩ በመሆን ለምርጫ ቀርበዋል፡፡
ዴሞክራቱ ካርተር በ1976 ምርጫ ጄራልድ ፎርድን በማሸነፍ ነበር ወደ ስልጣን የመጡት በነበራቸው አንድ የስልጣን ዘመን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና በኢራን ታግተው የነበሩ አሜሪካውን ጉዳይ ለአስተዳደራቸው ፈተና ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ባለ ሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት ፣ የወለድ ምጣኔ ከ 20 በመቶ መሻገር እና የጋዝ ዋጋ ማሻቀብ እንዲሁም የኢራን የእገታ ቀውስ በአሜሪካ ላይ ውርደትን ያመጡ ቀውሶች ተብለው ይታሰቡ ነበር፡፡
እነዚህ ጉዳዮች የካርተርን ፕሬዝዳንትነት አበላሽተው ለሁለተኛ ጊዜ የማሸነፍ ዕድላቸውን አሳጥተዋል።
በሌላ በኩል ለሰብአዊ መብት መከበር በነበራቸው ጠንካራ ሙግት እንዲሁም በ1978 በካምፕ ዴቪድ ስምምነት ግብጽ እና እስራኤል ሰላም እንዲፈጥሩ በማድረግ የኖቤል ሽልማትም አግኝተዋል፡፡
በወቅቱ በጦርነት ላይ የነበሩትን የሁለቱን ሀገራት ፕሬዝዳንቶች ወደ ካምፕ ዴቪድ በመጥራት የሰላም ስምምነት እንዲፈጽሙ ካደረጉ በኋላ እስራኤል ከሲናይ በርሀ ወታደሮቿን እንድታስወጣ ሀገራቱም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀምሩ አድርገዋል፡፡
የስልጣናቸውን የመጨረሻ 444 ቀናት ታጋቾችችን ለማስለቀቅ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመፍጠር በከፍተኛ ተጽዕኖ ውስጥ በሚገኙበት 1980 ለድጋሚ የስልጣን ዘመን ቢወዳደሩም በሪፐብሊካኑ ሮናልድ ሬገን በከፍተኛ ድምጽ ልዩነት ተሸንፈው ከሀላፊነት ተነስተዋል፡፡
ከ50 ግዛቶች በ44ቱ የተሸነፉት ፕሬዝዳንቱ በከፍተኛ ተቀባይነት ማጣት ከስልጣናቸው ቢለቁም በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ለብዙ አስርተ ዓመታት በትጋት ሠርተዋል።
እ.ኤ.አ. በ 2002 የኖቤል የሰላም ሽልማት የተሸለሙትም "ለአለም አቀፍ ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ፣ ዲሞክራሲን እና ሰብአዊ መብቶችን ለማስፈን እና ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትን ለማስፈን" ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በሚል ነው።
ካርተር በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ካስቆሙት የግብጽ እና እስራኤል ጦርነት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት ፣ የቦስኒያ እኛ የሄይቲ ግጭት እንዲቆም ከፍተኛ ሚናም እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል፡፡
ካርተር ከኋይት ሀውስ ከወጡ በኋላ ረጅም እድሜ ከኖሩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መካከል ቀዳሚው ናቸው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥር 9 በመላው የአሜሪካ የሀዘን ቀን ያወጁ ሲሆን በቀኑ መላው አሜሪካውያን ፕሬዝዳንቱ በማሳብ እንዲያሳልፉ ጠይቀዋል፡፡