የአዘርባጃኑ ፕሬዝደንት የተከሰከሰው አውሮፕላን ከሩሲያ ተተኩሶበት እንደነበር ተናገሩ
አውሮፕላኑ ከአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ 62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ሲበር ነበር ካዛኪስታን ውስጥ የተከሰከሰው
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ክሬሚሊን "ዘግናኝ አደጋ" ሲል ለገለጸው የአውሮፕላን አደጋ የአዘርባጃኑን ፕሬዝደንት አሊየቭን ይቅርታ ጠይቀዋል
የአዘርባጃኑ ፕሬዝደንት የተከሰከሰው አውሮፕላን ከሩሲያ ተተኩሶበት እንደነበር ተናገሩ።
በካዛኪስታን የተከሰከሰው እና ለ 38 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የመንገደኞች አውሮፕላን ሩሲያ ውስጥ ከመሬት ተተኩሶበት መጎዳቱን የአዘርባጃኑ ፕሬዝደንት ኢልሃም አሊየቭ በዛሬው እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ አሊየቭ በሩሲያ ውስጥ ያሉ "ውስን ቡድኖች" ስለአደጋው መንስኤ የተሳሳተ ትርክት በመንዛት የአዘርባጃኑ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ ምክንያት እንዳይታወቅ ለመሸፈን መሞከራቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ 62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ ሲበር ነበር ካዛኪስታን ውስጥ አክታው በተባለች ከተማ አቅራቢያ ከቀናት በፊት የተከሰከሰው።
አውሮፕላኑ ወደ ሩሲያዋ ቺቺኒያ ግዛት ዋና ከተማ ግሮዥኒ እያቀና ነበር።
ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ 38 መንገደኞች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን የቀሩት ደግሞ በህይወት ተርፈው በሆስፒታል ውስጥ የህክምና ክትትል እያደረጉ ናቸው ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ክሬሚሊን "ዘግናኝ አደጋ" ሲል ለገለጸው የአውሮፕላን አደጋ የአዘርባጃኑን ፕሬዝደንት አሊየቭን ይቅርታ ጠይቀዋል። የአዘርባጃኑ አውሮፕላን የተከሰከሰው የሩሲያ የአየር መከላከያ ስርአት የዩክሬን ድሮኖችን ለመምታት ተኩስ ከከፈተ በኋላ ነው ተብሏል።
የአዘርባጃኑ አውሮፕላን ከተከሰከሰ ከቀናት በኋላ እጅግ ከባድ የተባለ የመንገደኞች አውሮፕላን መከስከስ አደጋ በደቡብ ኮሪያ አጋጥሟል።
በዚህ አደጋ ከ181 መንገደኞች ውስጥ 179 የሚሆኑት የሞቱ ሲሆን የሀገሪቱ መንግስት የሰባት ቀናት የሀዘን ቀን ማወጁን አስታውቋል።