በዝቋላ ገዳም አራት የኃይማኖት አባቶች በታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ አራት አባቶች መገደላቸውን አስታውቃለች
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ግድያውን የፈጸመው “አሽባሪዉ ኦነግ ሸኔ” ነው ብሏል
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት የኃይማኖት አባቶች መገደላቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትናንት ባወጣቸው መግለጫ፤ “በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ አራት አባቶችን መግደሉን ገዳሙ አስታውቋል” ብላለች።
ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ታጣቂዎቹ ሦስት አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ከወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያርግበት ወቅት የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ አባቶችን በመያዝ ግድያ መፈጸሙን ቤተ ከርስርቲያኗ አስታውቃለች።
አባ ኪዳነማርያም ገብረሰንበት የተባሉት አባት ቆስለው በገዳሙ እንደሚገኙ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትናትን ባወጣችው መግለጫ፤ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ገዳማዊያኑንና ገዳሙን የመታደግ ሥራ እንዲሠሩ ጠየቀች።
ታጣቂዎቹ ወደ ገዳሙ ለመግባት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት መንገድ እንዳይኖርና መናንያኑና የገዳሙ ቅርስ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ገዳማዊያኑንና ገዳሙን የመታደግ ሥራ እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
የኦሮሚያ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫው “በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አገልጋይ የሆኑት አራት የገዳሙ አባቶች በአሽባሪዉ ኦነግ ሸኔ መገደላቸዉ ታውቋል” ብሏል።
የኃይማኖት አባቶች ላይ የተፈፀመዉ ግድያ የወረዳዉን ማህበረሰብ ያስደነገጠና በእጅጉ ያስቆጣ መሆኑን የቢሮውን መግለጫ ጠቅሶ ኦቢኤን ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅትም “የኦሮሚያ ለሰላምና ፀጥታ ቢሮናና ለፖሊስ የደረሰዉን ጥቆማ ተከትሎ አሽባሪዉን የማደን እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል” ብሏል መግለጫው።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን በአሸባሪ ኃይሉ ላይ በሚወሰደዉ እርምጃ የሚገኘዉን ዉጤት ለህዝብ በቀጣይነት የሚያሳዉቅ መሆኑንም አስታውቋል።