ፈረንሳይ በሩዋንዳው ዘር ጭፍጨፋ ‘የጎላ ሚና’ እንደነበራት የሚያመለክት የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ
በፍራንሷ ሚተራንድ ይመራ የነበረው የፈረንሳይ መንግስት ጭፍጨፋውን “አይቶ እንዳላየ” ማለፉንም ሪፖርቱ አመልከቷል
ሪፖርቱ ፈረንሣይ ለጭፍጨፋው እውን መሆን የ‘ተባባሪነት ሚና’ ነበራት ብሏል
በ100 ቀናት ውስጥ 800 ሺ ገደማ ቱትሲዎች በተጨፈጨፉበት የ1994ቱ የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ፈረንሳይ የተባባሪነት ሚና እንደነበራት የሚያመለክት የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ፡፡
የምርመራ ሪፖርቱ ይፋ የሆነው በሩዋንዳ መንግስት ቀጣሪነት ምርመራውን ባካሄደው ‘ሌቪ ፋይር ስቶን ሚዩዝ’ በተባለ አሜሪካዊ የምርመራ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ እ.ኤ.አ ከ2017 ጀምሮ ላለፉት 5 ዓመታት ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ የመጨረሻ ውጤት ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ሪፖርቱ ይፋ የሆነው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በመሩትና ዛሬ በተካሄደ ልዩ የሃገሪቱ ካቢኔ ስብሰባ ነው፡፡
ቦቢ ሚዩዝ የተባሉት የመርማሪው ተቋም ባልደረባም “A Foreseeable Genocide: The Role of the French Government in Connection with the Genocide against the Tutsi” በሚል ርዕስ የተካሄደውን ምርመራ የመጨረሻ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ባለ 600 ገጾች ጥንቅር ሆኖ የቀረበው ሪፖርቱ ፈረንሳይ ቱትሲዎች ሰለባ በሆኑበት ጭፍጨፋ የ‘ተባባሪነት ሚና’ እንደነበራት አስቀምጧል፡፡
“ተገማች የነበረው ጭፍጨፋ እውን እንዲሆን ፈረንሳይ ‘የጎላ ሚና’ ነበራት”ም ነው ሪፖርቱ ያለው፡፡
ሪፖርቱን ለማጠናቀር በሚሊዬን የሚቆጠሩ የሰነድ ማስረጃዎች ተመርምረዋል፡፡ የ250 ምስክሮች ቃልም ተደምጧል፡፡
በዚህም ፈረንሳይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሊፈጸም እንደሚችል ታውቅ ነበረ፡፡ መረጃውም ቀድሞ ነበራት፡፡
ሆኖም በፍራንሷ ሚተራንድ ይመራ የነበረው የፈረንሳይ መንግስት ጭፍጨፋውን “አይቶ እንዳላየ” አልፏል፡፡
ጭፍጨፋው እውን ከመሆኑ አስቀድሞ ከማስቆም ይልቅ ፈረንሳይ በሁቱዎች ይመራ ለነበረው የዩቬናል ሃብያ ሪማና መንግስት እና ለሩዋንዳ አጋሮቿ ድጋፍ ታደርግ እንደነበረም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
ጭፍጨፋውን የተመለከቱ “የሰነድ ማስረጃዎችን ከመሸሸግ ባለፈ ድርጊቱን ለማድበስበስ እና ለመሸፋፈን ሃሰተኛ ትርክቶችን በመፍጠር ጭምር ሲሰራ ነበር”ም ብሏል፡፡
ባለስልጣቶቿ በጭፍጨፋው ቀጥተኛ ተሳትፎ ስለማድረጋቸው ግን ሪፖርቱ አላረጋገጠም፡፡
ፈረንሳይ በጭፍጨፋው ሚና ነበራት የሚለውን አትቀበልም፡፡ ይህም ከሩዋንዳ ጋር አቃቅሯት ቆይቷል፡፡
ይህን ለመለየት ከአሁን ቀደም በፈረንሳዊው ታሪክ ተመራማሪ ቪንሶ ዱክለርት የተመራ ምርመራ ተካሂዷል፡፡
1 ሺ 200 ገጾች ያሉት የምርመራው የመጨረሻ ሪፖርትም ፈረንሳይ ምንም እንኳን ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችንና ጭፍጨፋውን በቸልታ ብታሳልፍም በጭፍጨፋው የተባባሪነት ሚና እንዳልነበራት ተመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ ለፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቀርቦ ማክሮን ሪፖርቱን ለሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ልከውም ነበረ ምንም እንኳን ሩዋንዳ በወቅቱ ሪፖርቱን እንደማትቀበል ብታስታውቅም፡፡
የአፍሪካ ህብረት ለዱክለርት ሪፖርት እውቅና መስጠቱ ይታወሳል፡፡