ለሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት የሆኑ “ምልክቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ እያየሁ ይህን መጽሃፍ አለመተርጎም…ጥፋት መስሎ ይታየኛል”
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ በሃገር በቀል እሴቶቻቸው በመታገዝ ሊታረቁና ሊሸማገሉ ይገባል
በሰሞነኞቹ ድርጊቶች “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አዝኛለሁ ኢትዮጵያውያን …ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ ያደረጉት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል”
ለሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት የሆኑ “ምልክቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ እያየሁ ይህን መጽሃፍ አለመተርጎም…ጥፋት መስሎ ይታየኛል”
በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ላይ ያተኮረውና በኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ የተጻፈው የ‘ሌፍት ቱ ቴል’ [Left to Tell, Discovering God Amidst the Rwandan Holocaust] መጽሃፍ ተርጓሚ ነው፡፡ “ሁቱትሲ፣ የወጣቷ ልብ አንጠልጣይ ትውስታዎች” በሚልም በ2008 ዓ/ም መጽሃፉን ተርጉሞታል፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ስነ ጽሁፍ መምህር እና በከተማዋ የሚገኘው የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻህፍት መስራችና ባለቤት የሆነው ወጣቱ ስራ ፈጣሪ መዘምር ግርማ፡፡
‘ሌፍት ቱ ቴል’ ለ3 ወራት የዘለቀውንና በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ 8 መቶ ሺ ገደማ ሩዋንዳውያን የተጨፈጨፉበትን መጥፎ ታሪካዊ አጋጣሚ ማጠንጠኛው አድርጎ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሃፍ ነው፡፡ መጽሃፉ በያዛቸው ታሪኮች ከመመሰጥ ባለፈ የደራሲዋን ሃዘን እየተጋራ አብሯት ሲፈራና ሲቸር፤ ሲጨነቅና ሲጠበብ ሲያዝንም ጭምር የነበረው መምህር መዘምርም ብዙዎች ሊማሩበት እንደሚችሉ በማሰብ ግሩም በሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡ ይህም ከሆነም እነሆ 5 አመታት አልፈዋል፡፡
መጽሃፉን ለምን ሊተረጉመው ቻለ?
‘ሌፍት ቱ ቴል’ን በሚያስተምርበት የዩኒቨርስቲ ቤተመጽሃፍት አግኝቶ ያነበበው መምህር መዘምር መጽሃፉ የተዋቀረባቸው አጽመ ታሪኮች እና ለዘር ማጥፋቱ ምክንያት የሆኑ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ መሆኑን ተከትሎ ለመተርጎም መነሳሳቱን ይናገራል፡፡
“እነዚህን ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥ እያየሁ ይህን መጽሃፍ አለመተርጎምና ለውይይት አለማብቃት ጥፋት መስሎ ነው የሚታየኝ”ም ነው የሚለው፡፡
“የተማርኩት የኢትዮጵያ ህዝብ በሚከፍለው ግብር ነው፤ ህዝቡን ለአደጋ ሊያጋልጠው የሚችልን ነገር እያየሁ ዝም ማለት የለብኝም፤ በመጽሃፉ የተጠቀሱ ስምንት የዘር ማጥፋት ሂደቶች ህዝቡን ከመከፋፈል እስከ ክህደት ጥፋቱን ከፈጸሙ በኋላ አልተካሄደም አለበለዚያም እንዲህ የሚባል ህዝብ አልነበረም እስከማለት ያሉት ሂደቶች ከሞላ ጎደል በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሞከሩና ዝግጅቶች እየተደረጉ ስለሆነ ብዙሃኑን ህዝብ ማስጠንቀቅ ተወያዩበት ማለቱ ግዴታዬ ስለሆነ መጽሃፉን ልተረጉመው በቅቻለሁ” ሲልም ያስቀምጣል፡፡
ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመተባበር ብዙዎች ሊማሩበት በሚችል መልኩ መጽሃፉን በኦሮምኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች ጭምር ለመተርጎም በመስራት ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ከሰሞኑ ለንባብ እንደሚበቃም ነው የተናገረው፡፡
“በሃገራችን የምናየው ነገር ባንፈልግ እንኳን ወደ አስከፊው የሩዋንዳ ሁኔታ ሊያስገባ የሚችል ዓይነት ነው” የሚልም ሲሆን ከግል የመታወቂያ ካርድ ጀምሮ እስከ የመኪና የሰሌዳ ቁጥሮች እንዲሁም ክልሎችን በዘር እስከማዋቀር የደረሱ ተግባራት ልዩነትን በሚያጎላ መልኩ መከናወናቸውን ይገልጻል፡፡
ይህ ደግሞ ለይቶ ለሚፈጸም ጥቃት የሚያጋልጥ ነው፡፡ በመሆኑም የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግና የብዙሃን መገናኛዎች አሰራር ሊፈተሽ እና ተቋማቱ ሙያዊ ስነ ምግባርን ጠብቀው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የሚናገረው፡፡
የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛዎች ሙያዊ ስነ ምግባርን ይጠብቁ ሲባል?
በሩዋንዳው የዘር ፍጅት ብዙሃን መገናኛዎች የጎላ [አሉታዊ] ሚና እንደነበራቸው የሚያነሳው ተርጓሚው “የእኛ ሃገር ሚዲያዎችስ ምን ዓይነት ናቸው?” ሲል ያጠይቃል፡፡
በሁቱ ጽንፈኞች ይመራ እንደነበረው አር.ቲ.ኤል.ኤም [RTLM] የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ሁሉ ተግባራቸው “በኢትዮጵያውያን መካከል ያሉ የዘርና የብሄር ልዩነቶችን ማስፋት አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ መቀስቀስ” የሆነ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም የማህበረሰብ የትስስር ገጾች እንደተበራከቱም ይናገራል፡፡
በእርግጥ ይህ ሙያን ያልተንተራሰና የረሳ የሚዲያዎቹ ተግባር በኢትዮጵያ መስተዋል ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በጊዜው ሃይ ሊባል ባለመቻሉም ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ ከሰሞኑ ያጋጠሙ ሁከትና ግርግሮችም ለዚሁ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሁከትና ግርግሮቹም ከ240 ያላነሰ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አጋጥሟል፤ ዜጎች የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡና የተረጋጋ ህይወትን እንዳይመሩም ሆኗል፡፡
መንግስትም ዘግይቶም ቢሆን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ያላቸውን ሚዲያዎች ተግባር በማውገዝ እስከመዝጋት የደረሰ እርምጃን ወስዷል፡፡
ቀጣይ ምን ይደረግ?
ሩዋንዳውያን ከአንድ መቶ አመታት በፊት ቅኝ ገዢዎቻቸው በነበሩት ቤልጂዬማውያን በተሰራው ዘርን መሰረት ያደረገ የመለያየትና ጽንፈኛ አቋምን የማስያዝ ስራ ነው ርስበርስ ዘር ለይተው ሁቱ ቱትሲ በሚል የተጨፋጨፉት፡፡
በሰሞነኞቹ ድርጊቶች “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አዝኛለሁ” የሚለው መዘምር “ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው በሚኖሩ፣ አብረዋቸው በሚበሉ እና በተዋለዷቸው ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ላይ ያደረጉት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል” ሲል ይናገራል፡፡
“ድርጊቱ የስልጣንም ይሁን ሌላ የጥቅም ፍላጎት ሊኖራቸው በሚችል ጥቂት አካላት የተቀናበረ ነው” ሲልም ነው የሚገልጸው፡፡ እነዚህ አካላት ልክ እንደ ሩዋንዳው ሁሉ መቶ የማይሞሉ ሊሆኑ እንደሚችሉም ግምቱን ያስቀምጣል፡፡ እነዚሁ አካላት “ከድርጊታቸው ሊታቀቡና በህግ ሊጠየቁ” ይገባልም ነው የሚለው፡፡
የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ በማቀድ በማስተባበርና በማስፈጸም ረገድ የጎላ ሚና ነበራቸው በሚል በአለም አቀፍ ደረጃ ተከሰው ለፍርድ የቀረቡት 62 ሰዎች ናቸው፡፡
ዘመናትን የተሻገረ የአብሮነትና የአንድነት እንዲሁም የመቻቻል ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከሩዋንዳውያኑ ሊማሩ እንደሚገባም ያሳስባል፡፡
“እኛ አብረን የኖርን ነን፤የጥላቻ ሃሳብ ለሚጠነስሱና አንዳችን በሌላችን ላይ እንድንነሳ፤ ጥቃት እንድንፈጽም ለሚያነሳሱን እና ለሚገፋፉን ሰዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ለህግ እንዲቀርቡ መተባበርም አለብን” ሲልም ኢትዮጵያውያን ጌጥ ሊሆኗቸው በሚችሉ ልዩነቶቻቸው እንዳይቃቃሩ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
ለዘመናት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ሊታረቁና ሊሸማገሉ እንደሚገባም ያነሳል፡፡ ለዚህም “ጋቻቻ” የተሰኘውን የሩዋንዳውያኑን ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓታት በተምሳሌትነት የሚጠቅስም ሲሆን በ“ጋቻቻ” ታግዘው መታረቃቸውንና የፍጅቱን ተዋናዮች ይቅር ማለታቸውን ያስቀምጣል፡፡
የካበተ ሃገር በቀል የእርቅና የሽምግልና እሴቶች ያሏቸው ኢትዮጵያውያንም በእሴቶቻቸው በመታገዝ ይቅር ሊባባሉና ያለፈውን ትተው ወደፊት ሊጓዙ፤አብሮነታቸውንም ሊያስቀጥሉ ይገባል እንደ መምህሩ ገለጻ፡፡
ከዓመት አመት ይበልጥ እየሰፉ በአይነትም በመጠንም እየተበራከቱ የመጡትን እንዲህ ዓይነቶቹን ህዝብን ለግጭት የሚዳርጉ ችግሮች ለማረም በተለይ ለውጥ እንደመጣ ከሚነገርባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ዘር እና ብሄርን መሰረት አድርገው ህዝብን ለማያባራ ሰላም እጦትና ቀውስ የዳረጉትን ችግሮች ለመፍታት ቃል ከመግባት ባለፈ ጠርዝ ረገጥ ልዩነቶች የወለዷቸውን ውጥረቶች ለማርገብ እንደሚያስችሉ የታመነባቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ አዳዲስ ህግጋት ወጥተዋል፤ አዳዲስ ተቋማትም ተመስርተዋል፡፡
የሃሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች አዋጅ ወጥቷል፤ ለማንነትና ለወሰን ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ ብሄራዊ እርቅንና ሰላምን ለማምጣት እንደሚሰሩ የታመነባቸው አዳዲስ ተቋማትም ተቋቁመዋል፤ ምንም እንኳን ተቋማቱ በቅርብ ጊዜ የተቋቋሙ መሆናቸውን ተከትሎ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል ተግባር አለመፈጸማቸው ቢነገርም፡፡