ሩዋንዳ የ1994ቱን የዘር ፍጅት 27 ኛ ዓመት መታሰብያ በዓል አከበረች
ተጎጂዎች በኮሮና ምክንያት በቤታቸው ሆነው የሚወዷቸውን ሰዎችን እያስታወሱ ነው
የዘር ፍጅት የመታሰቢያ በዓሉ ሻማ በማብራት ተከብሯል
ሩዋንዳውያን በፈረንጆቹ 1994 በቱሲዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል 27ኛ ዓመት የሰባት ቀናት መታሰቢያ ዛሬ ጀምረዋል፡፡ብዙዎች በኮቪድ-19 እገዳዎች ምክንያት በቤታቸው ውስጥ ሆነው የሚወዷቸውን ሰዎች በማስታወስ ላይ እንደሚገኙ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ዓመት በተከበረው የመታሰቢያ ዝግጅት ወቅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ብሔራዊ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ዣን ዳማሴኔ ቢዚማና፤ እያንዳንዱ መታሰቢያ የተለየ ቢሆንም በወረርሽኝ ወቅት ማዘን ግን ራስን ማዘጋጀት የሚፈልግ ነገር ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የዚህ ዓመት የመታሰብያ ስነ ስርዓትም የተለየ እንደማይሆን ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት፡፡
ምንም እንኳን የዘር ጭፍጨፋውን ለማስታወስ ሳምንታዊው መርሃግብር ይፋ ቢደረግም፣ በዚህ ዓመት የ 3 ቀናት ይፋዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ ይኖራሉም ብለዋል የኮሚሽኑ ዋና ፀሀፊ ዣን ዳማሴኔ ቢዚማና፡፡
ከኮሚሽኑ የተሰጠ መርሀ ግብር እንደሚያመለክተው ከሆነም፤ የመታሰብያ ስነ ስርዓቱ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ከዚያም በኪጋሊ የዘር ፍጅት መታሰቢያ የመታሰቢያ ሻማ በማብራት እንደሚከናወን ነው፡፡
የሚበራው ሻማ የመታሰቢያ ነጸብራቅ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች ክብር ለመስጠት እና ትዝታቸው አሁንም እንደቀጠለ እና ብሩህ እንደሚበራ ለማመልከት እንደሆነም ነው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤ.ኤፍ.ፒ/ የዘገበው፡፡
በመታሰብያ መርሀ ግብሩ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ዲፕሎማቶች እና ሌሎች የተመረጡ ታላላቅ ሰዎች ይሰበሰባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡