አሜሪካዊው የዓለማችን ባለጸጋ ኢሉን መስክ በሀብት መሪነት ደረጃቸውን ተነጠቁ
ፈረንሳዊው የፋሺን ነጋዴ በርናርድ አርናልት የዓለማችን ቀዳሚ ሀብታም ተብለዋል
የ73 ዓመቱ ፈረንሳዊ በ191 ቢሊዮን ዶላር የዓለማችን ባለጸጋ ተብሏል
አሜሪካዊው የዓለማችን ባለጸጋ ኢሉን መስክ በሀብት መሪነት ደረጃቸውን ተነጠቁ።
የቴስላ እና ትዊተር ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት ኢለን መስክ ላለፉት 14 ወራት የዓለም ባለጸጋነት ደረጃን ሲመሩ ነበር።
አሁን ላይ የዓለም ሀብታምነት ደረጃን ፈረንሳዊው የፋሺን ኢንዱስትሪ ሰው በርናርድ አርኖልት መቆጣጠራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የ73 ዓመቱ ፈረንሳዊ የሀብት መጠናቸው 191 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ያላቸው ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ጉዳት እየቀነሰ መምጣቱ ተጨማሪ ሀብት እንዲያገኙ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የ51 ዓመቱ ኢለን መስክ የሀብት መጠናቸው ወደ 185 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ ሲሆን ሁለተኛው የዓለማችን ሀብታሙ ሰው ተብለዋል።
ኢለን መስክ ከፈረንጆቹ መስከረም 2021 ጀምሮ ከአማዞን ኩባንያ ባለቤቱ ጄፍ ቤዞስ በመረከብ እስካሁን ድረስ የዓለማችንን ሀብታምነት ደረጃ ሲመሩ ቆይተዋል።
ኢለን መስክ ቴስላ የተሰኘው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያቸው ላይ የተወሰኑ ድርሻቸውን መሸጣቸው እና በትዊተር ኩባንያ ላይ ተጨማሪ ወጪ ማውጣታቸው ለሀብታቸው መቀነስ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የዓለም ባለጸግነት ደረጃን እስከ አስረኛ ድረስ ካሉት ሀብታም ሰዎች መካከል ስድስቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው።
ከፈረንሳዊው በርናርድ አርኖልት እና ኢለን መስክ በመቀጠል ህንዳዊው ጉዋታም አዳኒ ሶስተኛው የዓለማችን ሀብታሙ ግለሰብ ሲሆን ቢልጌት፣ ጄፍ ቤዞፍ፣ ዋረን ቡፌት እና ላሪ ኤሊሰን ቀጣዮቹን ደረጃዎች በቅደም ተከተላቸው ይዘዋል።