ተቋማቱ የተቀጡትን ገንዘብ በ3 ወር ውስጥ ገቢ ካላደረጉ በየእለቱ የ100 ሺህ ዩሮ ወለድ ይጠብቃቸዋል ተብሏል
ፈረንሳይ በግዙፎቹ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋማትበሆኑት ፌስቡክ እና ጎግል ላይ የ210 ሚሊየን ዩሮ ቅጣት ጣለች።
ፈረንሳይ ፌስቡክና ጎግል ላይ ቅጣቱን ያሳለፈቸው ሁለቱም ተቋማት ተጠቃሚዎቻቸውን መረጃ በሚሰበስቡብት “ኩኪስ” አሰጠቃቀማቸው ጋር ተያየዞ እንደሆነም ተነግሯል።
የግለሰቦችን የዳታ አጠቃቀም የመብት ጥሰትን የሚቆጣጠረው ሲ.ኤን.አይ.ኤል ሁለቱም ተቋማት የኢንተርኔት ተጠቃዎች በኦንላይን የግለሰቦችን መረጃ የሚሰበስቡ ኩኪዎችን መከልከል እንዳይችሉ አድርገዋል ብሏል።
ኩኪዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን መረጃ በመሰብሰብ ለማስታወቂያ አስነጋሪዎች መረጃ ለመስጠት የሚውል መሆኑ ይታወቃል።
የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በኩኪዎች አማካኝነት መረጃዎቻቸው እንዲሰበሰብ ፍቃድ የሚጠየቁ ሲሆን፤ ፍቀድ መቀበያ መንገዱም በጣም ቀላል መሆኑ ይታወቃል።
ሆኖም ግን ኩኪዎች መረጃዎቻችንን እንዳይሰበስቡ ማድረጊያ መንገድ አዳጋች ሲሆን፤ ይህም ልክ እንደመቀበሉ ሁሉ መከልከሉም ቀላል ሊሆን አንደሚገባ የግለሰቦችን የዳታ አጠቃቀም መብት የሚቆጣጠረው ሲ.ኤን.አይ.ኤል አስታውቋል።
ፌስቡክ እና ጎግልም ሰዎች ኩኪዎችን ሲቀበሉ ቀላል እንደሆነ ሁሉ እምቢ ማለት ሲፈልጉ ግን አዳጋች አድርገዋል በሚል ነው በፈረንሰይ የተቀጡት።
በዚህም መሰረት ጎግል ላይ የ150 ሚሊየን ዩሮ እንዲሁም ፌስቡክ ላይ ደግሞ በ60 ሚሊየን ዩሮ በድምሩም የ210 ሚሊየን ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
ሁለቱም ተቋማት የተላለፈባቸውን የገንዘብ ቅጣት በ3 ወር ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ያዘዘችው ፈረንሳይ፤ ገንዘቡን በተቀመጠው ጊዜ ገቢ ካላደረጉ የቅጣት ገንዘቡ በየእለቱ የ100 ሺህ ዩሮ ወለድ እንደሚኖረውም አስታውቃለች።