ሮሂንጋዎች ከምያንማር የጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ ፌስቡክን በ150 ቢሊየን ዶላር ከሰሱ
በአሜሪካና በብሪታኒያ ውስጥ የሚገኙ የሮሂንጋ ስደተኞች ፌስቡክን ከሰዋል
የምያንማር በአውሮፓውያኑ 2017 በተደረገ ወታደራዊ ዘመቻ ከ10 ሺህ የሚልቁ ሮሂንጋዎች ተገድለዋል
በአሜሪካ እና በብሪታኒያ የሚገኙ በርካታ የሮሂንጋ ስተደኞች በምያንማር ሲካሄድባቸው የነበረው የጥላቻ ንግግር እንዲሰራጭ ፈቅዷል ያሉትን ፌስቡክ መክሰሳቸው ተገለፀ።
ፌስቡክ በምያንማር ውስጥ አነስተኛ ማህበረሰብ በሆኑት ሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የጥላቻ ንግግሮችን በማበረታታቱ ልጥፎችን በማበረታታቱ ቢያንስ የ150 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ካሳ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል።
በብሪታኒያ የሮሂንጋ ስደተኞችን ወክሎ እየተከራከረ ያለው የህግ ተቋም ለክባንያው በጻፈው ደብዳቤ፤ የፌስቡክ በሮሂንጃዎች ላይ የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታዩ ማድረጉን አስታውቋል።
ፌስቡክ በሮሂንጋ ላይ ሁከት የሚቀሰቅሱ ፅሁፎችን ከገጹ አለማስወገዱን እንዲሁም ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡትም "ተገቢ እና ወቅታዊ እርምጃ" መውሰድ እንዳልቻለም አመላክቷል።
ሌላኛው በፌስቡክ የወጣ ፅሁፍ እንዲሁ "ነዳጅ አፍስሱና እሳት ለኩሱባቸው ፈጣሪያቸውን በፍጥነት ይገናኛሉ" የሚሉ እንደሚገኙበትም ቢቢሲ ከጠበቆቹ ያገኘውን ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በቅርቡ ስያሜውን ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ ኩባንያ በሮሂንጋ ስደተኞች ለቀረበበት ክስ እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱም ነው የተነገረው።
ፌስቡክ በአውሮፓውያኑ 2018 በሮሂንጋ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል በቂ ስራ አለመስራቱን አምኖ እንደነበረ ይታወሳል።
ሮሂንጋዎች በምያንማር ውስጥ እንደ ህገ ወጥ ስደተኞች ስለሚታዩ በሀገሪቱ መንግስት እና ህብረተሰብ ዘንድ ለበርካታ አስርት ዓመታት በርካታ መገለሎች ሲደርሱባቸው እንደነበረ ይነገራል።
በአውሮውያኑ በ2017 የሮሂንጋ ሚሊሻዎች በምያንማር ፖሊስ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ፤ የሀገሪቱ ጦር በራክሂን ግዛት በነበሩ ሮሂንጋዎች ላይ እርምጃ እንደወሰደባቸው ይታወሳል።
የምያንማር ጦር በ2017 በወሰደው እርምጃም ከ10 ሺህ በላይ የሮሂንጋ ሙስሊሞች መገደላቸው እና በርካቶችም ለስደት መዳረጋቸው አይዘነጋም።