ምዕራባውያን ዜጎቻቸውን ከሶሪያ እንዲያስወጡ ተጠየቀ
በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ በርካታ የፈረንሳይ ህጻናት እንዳሉ ተገልጿል
ፈረንሳይ በሶሪያ የነበሩ ህጻናትና እናቶችን ማስመለሷን አስታወቀች
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ምዕራባውያን ሀገራት በሶሪያ የሚገኙ ዜጎቻቸውን እንዲያስወጡ ጠየቁ፡፡
ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ባለፈም በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ጦር በሶሪያ ዜጎች ያሏቸው ሀገራት በአስቸኳይ ማስወጣት እንዳለባቸው ጠይቋል፡፡
እስላሚክ ስቴትን ለመቀላቀል የሄዱ ወይንም በጦርነቱ ጊዜ በሶሪያ የተወለዱ ዜጎቻቸውን መመለስ እንዳለባቸው ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ይህንን ተከትሎም ፈረንሳይ በሶሪያ የነበሩ ከ 50 በላይ ዜጎቿን ማስመለሷን አስታውቃለች፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን 35 ሕጻናትና 16 እናቶች ከሶሪያ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልጿል፡፡ ፈረንሳይ ዜጎቿን የመለሰችው በሶሪያ ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሆነም ነው ያስታወቀችው፡፡
ወደ ፈረንሳይ እንዲመለሱ የተደረጉት ዜጎች በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የነበሩ መሆናቸውንም ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡ ህጻናቱ ቻይልድ ዌልፌር አገልግሎት በሚባል ተቋም የተመለሱ ሲሆን የሕክምና ክትትል እንደሚደረግላቸውም ይጠበቃል፡፡
ፓሪስ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ትብብር እንደተደረገላትም ገልጻለች፡፡ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ዜጎቹን በማስመለሱ ሂደት ተባባሪ ለነበሩት የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ አካባቢ አስተዳዳሪዎች ምስጋና አቅርቧል፡፡
የሽብር ጥቃት ይደርሳል በሚል ፍራቻ ፈረንሳይ በሶሪያ ያሉ ዜጎችን በብዛት ለመመለስ ፍቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች፡፡ በሀገሪቱ መዲና ፓሪስ እ.አ.አ በ 2015 የደረሰውና ለ130 ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነው የሽብር ጥቃት ፓሪስን ለሽብር ትኩረት እንድትሰጥ አድርጓታል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ የፈረንሳይ ህጻናት የምግብ ችግርና የጤና ችግር ባለበት የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ግዛት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ህጻናቱ ያሉቡት ቦታ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነም ተገልጿል፡፡