በሶስት ሴቶች የአስገድዶ መድፈር የተጠረጠሩት የቀድሞው የውህደት ሚኒስትር በአዲሱ ካቢኔ አልተካተቱም
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ ካቢኔ ማዋቀራቸው ተስመቷል።
ባሳለፍነው ግንቦት አጋማሽ ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አድርጋ ኢማኑኤል ማክሮንን ለሁለተኛ ጊዜ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርጋ የመረጠችው ፈረንሳይ አሁን ደግሞ የሕግ አውጭዎች ምክር ቤት ምርጫ ማካሄዷ ይታወሳል።
በዚህ ምርጫ ላይ የፕሬዝዳንት ማክሮን ፓርቲ በምክር ቤቱ የአብላጫ ወንበርን ለተቀናቃኛቸው ቀኝ እና ግራ ዘመም ፓርቲዎች ህብረት አሳልፈው መስጠታቸውም አይዘነጋም።
የምርጫውን ውጤት ተከትሎም ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ ካቢኔያቸውን ያዋቀሩ ሲሆን በእንደራሴዎች ምክር ቤት ምርጫ የተሸነፉ ሚኒስትሮችን በአዲስ ተክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፍራንሲስ ብራውን የጤና ሚኒስትር ፣ክርስቶፈር ብቹ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር፣ ላውረንስ ቦኔ የአውሮፓ ሚኒስትር እንዲሁም ክሌምንት ቡኔ ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሸመዋል፡፡
የባህር ብዝሃ ህይወት ሚኒስትር ደግሞ ሄርቪ ቤርቪል ሆነው ሲሾሙ ጂያን ክሪስቶፍ የማህበራዊ እና ውህደት ሚኒስትር ተደርገው መሾማቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
በሶስት ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተጠረጠሩት እና የቀድሞው የአሚማኑኤል ማክሮን ካቢኔ አባል የነበሩት ዳሜን አባድ ከአዲሱ ካቢኔ ውጪ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡
የፈረንሳይ የሕግ አውጪ ምክር ቤት 289 መቀመጫ ያለው ሲሆን ተቃዋሚዎች 245 መቀመጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ምርጫ የግራ ዘመም ፓርቲዎች ህብረት 131 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ሲያሸንፉ በማሪን ለፐን የሚመራው ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ህብረት ደግሞ 89 መቀመጫዎችን እንዳሸነፉ ተገልጿል፡፡