ፈረንሳዊው ኮከብ ቲየሪ ሄንሪ በዘረኝነት ምክንያት ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም አቆማለሁ አለ
“ዘረኝነት መርዛማ ነው” እናም የተወሰነ ተጠያቂነት መኖር አለበትም ብሏል ቲየሪ ሄንሪ
የእንግሊዝ እግር ኳስ የበላይ አካላት የማህበራዊ አውታር መረቦች “የመጎሳቆል መጠልያዎች” ናቸው ማለታቸው ይታወሳል
የእግር ኳስ ኮከቡ ቲየሪ ሄንሪ “በዘረኝነት ምክንያት” ማህበራዊ ሚዲያውን መጠቀም እንደሚያቆም አስታወቀ፡፡
በአለማችን ከታዩ ድንቅ የፊት መስመር አጥቂዎች አንዱ የሆነው ፈረንሳዊው ኮከብ ቲየሪ ሄንሪ ማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶቹን መጠቀም የሚያቆመው፤ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተከፈቱና ዘረኝነትን በሚረጩ አካውንቶች ላይ እርምጃ አለመወሰድን ለመቃወም እንደሆነም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
በፌስቡክ፣ኢንሰታግራም እና ትዊተር አካውንቶቹ ብቻ ከ15 ሚልዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የቀድሞ የአርሰናልና ባርሴሎና የፊት መስመር አጥቂው ቲየሪ ዳንኤል ሄንሪ፤ የማህበራዊ ሚድያ ፕላትፎርሞቹ መሰል የዘረኝነት ጉዳዮች ለመቅረፍ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡
“በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች አሠራራቸው ማስተካከል እስኪችሉ ድረስ ከነገ ጠዋት ጀምሮ ራሴን ከማህበራዊ አውታር መረቦች እለቃለሁ”ያለው የእግር ኳስ ኮከቡ ቲየሪ ሄንሪ በግለሰቦች ላይ የሚደርሰው ዘረኝነት፣ የጉልበተኝነት ጫና እንዲሁም በዚህ ምክንያት በአእምሮ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ችላ ማለት በጣም መርዛማ ነው እናም የተወሰነ ተጠያቂነት መኖር አለበት ሲል አስታየቱን ሰንዝረዋል፡፡
ሄንሪ፡“ ማንነታቸው ያልታወቁ አካውንቶች በመክፈት ሌሎችን መተንኮስና ጫና ማሳደር ቀላል ነው፤ እናም ይህ አሰራር እስካልተቀየረ ድረስ ሁሉም የአካውንት ፕላትፎርሞች የማልጠቀም ይሆናል፡፡ በቅርቡ እንደሚሰተካከልም ተስፋ አደርጋለሁኝ” በማለትም አክሏል፡፡
ባለፈው ወር የእንግሊዝ እግር ኳስ የበላይ አካላት ትዊትር፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የመሳሰሉ የማህበራዊ አውታር መረቦች “የመጎሳቆል መጠልያዎች” ናቸው ብለው መተቸታቸውንና ፤የማህበራዊ ሚድያ ኩባንያዎች በእግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ በተለያዩ ጊዝያት ሲሰነዘሩ የሚስተዋሉ ‘የዘረኝነት መልእከቶች’ ለመከላከል በሚቻልበት ዙርያ መስራት አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
እግር ኳሱ በላይ አካላት ማሰሰብያን ተከትሎም፤ መሰል ተግባር ላይ በሚሰማሩ ግለሰቦች ላይ አካውንት አስከ መዝጋት እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቅያ በመስጠትም ኢንታግራም ቀደሚ የማህበራዊ አውታር መረብ ነው፡፡