ፈረንሳይ ለሱዳን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ልታበድር ነው
የፈረንሳይ መንግስት እንዳስታወቀው ሱዳን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከፈረንሳይ ታገኛለች
ብድሩ ሱዳን የዓለም አቀፉ የፋይናነስ ተቋም (IMF) ያለባትን ውዝፍ እዳ ለመክፈል ያለመ ነው ተብሏል
የብድር ስምምነቱን ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የሱዳኑ ጠ/ሚ አብደላ ሀምዶክ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።
ጠ/ሚ አብደላ ሱዳን በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አገራቸው ያለባትን ብድር ጫና መቀነስ የሚያስችሉ ስምምነቶች እንደሚፈረሙ እጠብቃለሁ ብለዋል።
ሱዳን ከተለያዩ የዓለማችን አገራት እና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት 50 ቢሊዮን ዶላር እዳ ያለባት ሲሆን የብድር ጫናው ከዓመታዊ ምርቷ 38 በመቶ ይሸፍናል።
የብደር እዳ ማቃለያ አርምጃዎች የሱዳን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ያግዘናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ሱዳን በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ ከቆየችበት ሽብርተኞችን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር መውጣቷ እና ተጥለውባት የነበሩ ማዕቀቦች የተሰረዙላት መሆኑ ይታወሳል።
ሃምዶክ “እኛ የምንፈልገው የወረቀት ላይ ስምምነቶችን ሳይሆን እውነተኛ ኢንቨስትመንቶችን ነው” ሲሉ ዘ ናሽናል ለተሰኘው ሚዲያ ተናግረዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ለመደገፍ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በፈረንሳይ ፓሪስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የፋይናንንስ እና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
የሩዋንዳውን ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜን እና የግብጹን ፕሬዘዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጨምሮ ሌሎች አፍሪካዊ መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉም ተብሏል።