ሃገራት ‘የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በርካሽ እናቀርባለን’ በሚሉ አካላት እየተጭበረበሩ ነው ተባለ
ኢንተርፖል ሃገራት ሊጠነቀቁ እንደሚገባም ነው ያሳሰበው
እስካሁን 40 ሃገራት የአጭበርባሪዎች ሰለባ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም አስታውቋል
የተደራጁ ወንጀል ቡድኖች ሃገራትን ‘እውነተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በርካሽ እናቀርባለን’ በሚል እያጭበረበሩ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) አስታወቀ፡፡
የወንጀሉን መበራከት አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ኢንተርፖል መንግስታት እንዲጠነቀቁ አሳስቧል፡፡
ኢንተርፖል በሃገራችሁ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ያገኙ እውነተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በርካሽ እናቀርባለን በሚሉ ወንጀለኞች የተጭበረበሩ የወንጀሉ ሰለባዎችን በ40 የዓለማችን ሃገራት በሚገኙ 60 የጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ሆስፒታሎች ማግኘቱን ተከትሎ ነው ማሳሰቢያውን የሰጠው፡፡
አጭበርባሪዎቹ ክትባት አምራች ኩባንያዎችን ወይም የመንግስታት የክትባቶቹ አመቻች ዐይነት ሆነው ነው እውነተኛ በሚመስሉ የኢ-ሜይል እና የስልክ የግንኙነት መንገዶች የሚቀርቡት፡፡ ሃሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ እና የድረገጽ አድራሻዎችንም ይጠቀማሉ፡፡
ይህ በገሃዱ ዓለም የሌሉና ያልተመረቱ፤ ፈቃድም ጭምር ያላገኙ ሃሰተኛ ክትባቶችን ለመሸጥና የሳይበር ጥቃቶችን ለመፈጸም ያስችላቸዋል እንደ ኢንተርፖል ዋና ጸሃፊ የርገን ስቶክ ገለጻ፡፡
የርገን ድርጅታቸው ከመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች በደረሰው ጥቆማ መሰረት ለ194 አባል ሃገራቱ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡
እንዲህ ዐይነት ነገር የገጠማቸው ሁሉ በየአካቢያቸው ለሚገኙ የፖሊስ አካላት ሪፖርት እንዲያደርጉም ነው ዋና ጸሃፊው የጠየቁት፡፡
የአውሮፓ ፖሊስ ባሳለፍነው ሳምንት የፊት መሸፈኛ ጭምብልን (ማስክ) መሰል ወረርሽኙን የመከላከያ የህክምና ቁሳቁሶች በሃሰተኛ ኩባንያዎች ስም ሲሸጡ አግኝቻለሁ ባላቸው 23 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ዘ ናሽናል ዘግቧል።
ዘ ናሽናል አጭበርባሪዎች እስካሁን በሮማኒያ የባንክ ሂሳቦች አማካይነት የተላከ ከ1 ሚሊዮን ዩሮ (1.2 ሚሊዮን ዶላር) በላይ ገንዘብን እንዳገኙ ይገመታልም ነው ያለው።