የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከ100 ሚሊየን በላይ ሰራተኞችን ደሃ አድርጓል- ተመድ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቶች የስራ እድል በ8 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል
የአብዛኛው ሰራተኞችና የቤተሰቦቻቸው የእለት ገቢ በአማካይ ከ3 ዶላር በታች ነው
ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ከ100 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ደሃ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አደረገ።
ወረርሽኙን ተከትሎ የስራ ሰዓቶች መቀነስ እና ጥሩ ስራ የማግኘት እድል መቀነስ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት (አይ ኤል ኦ) በሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ በዘርፉ የተስተዋለው ቀውስ የሰራተኞች ገቢ በጣም እንዲያሽቆለቁል በማድረግም ድህነት ከፍ እንዲል አድርጓል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ከነበረው ጊዜ ጋር ሲነጻጸርም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ 108 ሚሊየን ሰራተኞች ወደ ድህነት መግባታቸው ተመላክቷል።
ይህ ሰራተኞቹ እና ቤተሰቦቻቸው ከ3 ዶላር በታች ገቢ እንደሚያገኙ እና ኑሮዋቸውንም በዚሁ ለመግፋት እንደሚገደዱ የሚያሳይ ነው።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቶች የስራ እድል በ8 ነጥብ 7 በመቶ የቀነስ ሲሆን፤ እድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች ስራ የማግኘት እድል ደግሞ በ3 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ አስይቷል።
በዓለማችን ላይ እስከያዝነው የፈረንጆች 2021 መጨረሻ ድረስ 75 ሚሊየን የስራ እጥረት እንደሚከሰትም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።
ወረርሽኙ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ እስከ ቀጣይ ዓመት መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 23 ሚሊየን የስራ እጥረት እንደሚከሰትም ነው የተገለጸው።
የዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ኃላፊ ገይ ረይደር፤ “ኮቪድ 19 በጤናው ዘርፍ ብቻ አይደለም ችግር ያስከተለው፤ በስራ እና በሰዎችም ላይ ነው” ብለዋል።
በተለየ ጥረት እና ትኩረት ተሰጥቶበት ካልተሰራ ወረርሽኙ መቆየቱ ስለማይቀር በስራው ዘርፍ የሚፈጠረው ችግር እንደሚጨምር እና ወደ ድህነት የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እንደሚጨምርም አስታውቀዋል።