አገሪቱ ጦሯን ለማስወጣት የወሰነችው ማሊ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ማሰማራቷን ተከትሎ ነው
ስዊድን በፈረንሳይ መሪነት በማሊ ያሰማራችውን ጦር እንደምታስወጣ ገለጸች፡፡
ስዊድን በምዕራብ አፍሪካ ከተሰማራው የአውሮፓ ልዩ ሀይል ጋር ወታደሮችን ካዋጡ አገራት መካከል አንዷ ነበረች፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በሳህል ቀጠና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተሰማራው የአውሮፓ ልዩ ሃይል ስዊድንን ጨምሮ ከ14 የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የተውጣጣ ነው፡፡
ይህ ጦር በፈረንሳይ አስተባባሪነት የሚመራ ሲሆን ዋና ተልዕኮው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ ነበር፡፡
ይህ ጦር ዋና መቀመጫውን በማሊ ልዩ ስፍራው ታኩባ በሚባል ቦታ ሰፍሮ በማሊ እና በሌሎች በሳህል ቀጠናዎች ሲንቀሳቀስ ሰንብቷል፡፡
የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ስዊድን ጦሯን ለማስወጣት መወሰኗን ተሰብሳቢዎች መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ስዊድን በተለያዩ ጊዜያት በፈረንሳይ መሪነት በምዕራብ አፍሪካ እና 5 ሺህ ጦር አባላት ላሉት ጦር 400 ጦር አዋጥታ ነበር፡፡
ይሁንና ማሊን ጨምሮ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት በፈረንሳይ አስተባባሪነት በሚመራው ጦር ደስተኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ጦር ያዋጡ የአውሮፓ አገራት ጦራቸውን ለማስወጣት በመወሰን ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የማሊ ወታደራዊ መንግስት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ወደ አገሩ በማስገባቱ ምክንያት ክስተቱ ፈረንሳይን ጨምሮ በአካባቢው ጦራቸውን የላኩ አገራትን አበሳጭቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የማሊ ወታደራዊ መንግስት ምርጫ አካሂዶ ስልጣኑን ለሲሰቪል አስተዳድር ካላስረከበ ማዕቀብ እንደሚጥል አስጠንቅቋል፡፡