ምዕራብ አፍሪካ አገራት በማሊ ያሉ አምባሳደሮቻቸውን ሊጠሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮዋስ በማሊ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጣለ።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ባለፉት ሁለት ዓመታ ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህብረሰብ ወይም ኢኮዋስ ከዚህ በፊት ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው የማሊ ጁንታ ምርጫ የሚያደርግበትን ጊዜ አዲሱ የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከመግባቱ በፊት ምርጫ የሚያካሂድበትን እቅድ እንዲያሳውቅ ጠይቆ ነበር።
በ40 ዓመቱ ኮለኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ጁንታ ወታደራዊ መንግስት ምርጫ ለማድረግ እና ስልጣን በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ለማስረከብ አምስት ዓመት ከስድስት ወር ያስፈልገኛል ብሏል።
በማሊ ጁንታ ምላሽ የተበሳጨ የመሰለው ኢኮዋስ የምርጫ ማድረጊያ እቅዱ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብሏል።
የማሊ ጁንታ ምርጫ የሚያደርርበትን እቅድ ድጋሚ እንዲያጤነው ያስጠነቀቀው ኢኮዋስ፤ ይህ ካልሆነ ግን በማሊ ያሉ አምባሳደሮቻቸውን እንደሚያስወጡ፣ ከማሊ ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበራቸውን እና የአየር ክልላቸውን እንደሚዘጉ አስጠንቅቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከማሊ ጋር የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን ከማገድ ጀምሮ ሌሎች የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ሊያደርጉ እንደሚችልም የኢኮዋስ አባል አገራት ገልጸዋል።
የማሊ ጁንታ ከሁለት ዓመት በፊት በምርጫ አሸንፈው የአገሪቱ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቡበከር ኬታን በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል።