ፈረንሳይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ለነበራት ሚና ሩዋንዳን ይቅርታ ጠየቀች
ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ፈረንሳይ ሚና እንደነበራት አረጋግጠዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት “ሩዋንዳውያን የይቅርታን ስጦታ ስጡን” ብለዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ድርጊት ሀገራቸው ሚና እንደነበራት አረጋገጡ።
ፕሬዝደንት ማክሮን በሩዋንዳ የሚያደርጉትን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኘት በዛሬው እለት ጀምረዋል።
ፕሬዝደንቱ በኪጋሊ በሚገኘው ጊሶዚ የተባለ ከ250 ሺህ በላይ ቱትሲዎች የተቀበሩበት የሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ስፍራ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ከ27 ዓመታት በፊት ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሚና እንደነበራት አረጋግጠዋል።
“ፈረንሳይ በወቅቱ የዘር ጭፍጨፋ ሊፈጸም ይችላል በሚል ሲያስጠነቅቁ የነበሩ አካላትን ችላ በማለት ፣ የዘር ፍጅት ከፈጸመው መንግስት ጎን ቆማለች” ሲሉም ተናግረዋል።
“በዚያን እለት በዚህ ጎዳና ላይ ያለፉትን ይቅር ማለት ብቻ ነው የሚቻለው፣ የይቅርታን ስጦታ ስጡን” ሲሉም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩዋንዳውያንን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ፣ የፕሬዝደንት ማክሮንን ይቅርታ “ከፍተኛ ትርጉም ያለው” ብለው የገለጹ ሲሆን ይቅርታቸውን በአድናቆት ተቀብለዋል፡፡
በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ 800 ሺህ ገደማ ቱትሲዎች በተጨፈጨፉበት የ1994ቱ ጭፍጨፋ ፈረንሳይ ምን ሚና እንደነበራት ለመለየት የተካሄደውን ምርመራ እንደምትቀበል ሩዋንዳ ማስታወቋ ይታወሳል።
ምርመራው 15 ፈረንሳውያን አባላት ባሉት እና በፕሬዝዳንት ማክሮን በተቋቋመው የምርመራ ኮሚሽን ነው የተካሄደው።
በፍራንሷ ሚተራንድ ትመራ የነበረችው ፈረንሳይ የሩዋንዳው ዩቬናል ሃብያ ሪማና መንግስት ደጋፊ እንደነበረች ይነገራል።
በዚህም ለጭፍጨፋው ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችን አይቶ እንዳላየ ከማለፍም በላይ አላስቆመችም በሚል በጭፍጨፋው ተባባሪነት ጭምር ትወቀሳለች።
የሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትም በዚሁ ምክንያት ሻክሮ መቆቱ አይዘነጋም።