የፈረንሳይ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አባያ የለበሱ ተማሪዎችን እየመለሱ ነው ተባለ
በሀገሪቱ ትናንት ትምህርት ሲጀመር 300 የሚጠጉ ተማሪዎች አባያ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤቶች አቅንተዋል

ፓሪስ ባለፈው ሳምንት በትምህርት ቤቶች ውስጥ አባያ እንዳይለበስ መከልከሏ ይታወሳል
ፈረንሳይ 300 የሚጠጉ ተማሪዎች አባያ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤቶች መግባታቸውን ገለጸች።
የሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር፥ በትምህርት ቤቶች አባያ እንዳይለበስ ቢከለከልም ትናንት 298 ተማሪዎች ለብሰውት ገብተዋል ብሏል።
አብዛኞቹ ተማሪዎች ከእንግዲህ አለባበሳቸውን ለማስተካከል ተስማምተው ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን አስታውቋል።
67 ተማሪዎች ግን ክልከላውን በመቃወማቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል ነው የተባለው።
ከተማሪዎቹ ወላጆች ጋር በሚደረግ ውይይት መግባባት ካልተቻለም ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታቸው ለመራቅ እንደሚገደዱ ሬውተርስ ዘግቧል።
በፈረንሳይ ከ5 ሚሊየን በላይ ሙስሊሞች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሴቶች የሚለብሱት አባያ በትምህርት ቤቶች እንዳይለበስ መከልከሉም ተቃውሞ ሲያስነሳ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ 12 ሚሊየን ወንድ እና ሴት ተማሪዎች ትናንት ትምህርት ሲጀምሩ የታየው አፈጻጸም ክልከላው ተቀባይነት ማግኘቱን ያሳያል ብሏል የሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር።
የተወሰኑ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችን የወከሉ የህግ ባለሙያዎች ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ወስደውታል።
ፈረንሳይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች እና የመንግስት ህንጻዎች ላይ ሃይማኖታዊ ምልክቶች እንዳይታዩ የሚከለክል ጠንከር ያለ ህግ አላት።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ክልከላዎችን የጣለችው ፓሪስ በተለይም ከ2004 ወዲህ በሙስሊም ሴቶች ላይ ጠንከር ያሉ ውሳኔዎች አሳልፋለች።
ትልልቅ መስቀል ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ እምነቶችን ያንጸባርቃሉ የሚባሉ ምልክቶች በመንግስት ተቋማት መታየት የሌለባቸው የመንግስት እና ሃይማኖት መለያየትን ለማሳየት ትላለች ፓሪስ።