ታሊባን የአፍጋኒስታን ሴቶች ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ አገደ
የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሴቶችን እንዳይቀበል የሚል መመሪያ አውጥቷል
የታሊባን አስተዳደር ውሳኔ ተመድን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና ተቋማት እየተቃወሙት ነው
አፍጋኒስታንን ከሁለት አስርት በኋላ ዳግም እያሰተዳደረ የሚገኘው ታሊባን ሴቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ አግዷል።
የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው ደብዳቤ እንደሚያሳየው የተለይ ትዕዛዝ እስኪመጣ ድረስ የመንግስትም ሆነ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሴቶችን ተቀብሎ ማስተማር አይችሉም።
የታሊባን አስተዳደር ካቢኔ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአፍጋኒስታን ጉዳይ ለመምከር ቀጠሮ በያዘበት እለት ነው።
ተመድ፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያ ዳግም ስልጣን የተቆናጠጠው ታሊባን የሴቶችን መብት ያሻሽላል ተብሎ ሲጠበቅ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት እስከማገድ የደረሰ ውሳኔ ማሳለፉን ተቃውመውታል።
ውሳኔን የመንግስታቱ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና ተቋማት እየተቃወሙት ነው
ታሊባን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ይሁንታን ያገኝ ዘንድ የአፍጋኒስታናውያንን ሰብአዊ መብትና በተለይ የሴቶችን ነጻነት ሊያከብር ይገባል ብለዋል በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ ረዳት አምባሳደር ሮበርት ዉድ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስም ዋሽንግተን ታሊባንን ተጠያቂ ለማድረግ እያጤነች ነው ማለታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
በተመድ የብሪታንያ አምባሳደር ባርባራ ውድዋርድ በበኩላቸው፥ የታሊባን ውሳኔ በየትኛውም አካባቢ የምትገኝን ሴት የሚያስከፋ የሰብአዊ መብት ገፈፋ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በመጋቢት ወር 2022 ሴቶች ብቻ የሚማሩበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እከፍታለሁ የሚል ቃል የገባው ታሊባን፥ አሁን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴቶችን እንዳያስተናግዱ አሳስቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ በኒዮርክ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ታሊባን የሚገባውን ቃል ማፍረሱን ገፍቶብታል፤ ሀገሪቱን ያለ ሴቶች ተሳትፎ እንዴት ሊመራት እንዳቀደም ማሰብ ይከብዳል ብለዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአፍጋኒስታን ልዩ መልዕክተኛ ሮዛ ኦቱንባየቫ የካቡልን ውሳኔ እንደሰሙ በጸጥታው ምክር ቤት ባሰሙት የተቃውሞ ድምጽ፥ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ታሊባንን መታገስ አብዝቷል ነው ያሉት።
ታሊባን የሴቶችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ እንዲታገድ ያዘዘው ተማሪዎች ለፈተና ዝግጅት ላይ እያሉ ነው።
በርካታ ተማሪዎችም ይህን ውሳኔ በመስማታቸው በከፍተኛ መረበሽ ውስጥ መሆናቸውን ነው ሬውተርስ ያነጋገራቸው አፍጋናውያን የተናገሩት።
ታሊባን በመስከረም ወር 2021 የአሜሪካ መራሹ ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ስልጣን ዳግም ይዟል።
መንግስት ሆኖ ሀገር እየመራ ያለው ታሊባን በሴቶች መብት ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ቢገልጽም ሴቶች በፓርኮች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዳይገኙ የሚያስገድድ መመሪያ ሲያወጣ ጊዜ አልወሰደበትም።