ታሊባን ሴቶች በመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት እንዳይሰሩ መከልከሉ ተመድን አስቆጥቷል
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፥ የታሊባን ውሳኔ የሴቶችን መሰረታዊ መብት የሚገፍ ነው በሚል በጽኑ ተቃውመውታል
ታሊባን ከዚህ ቀደምም ሴቶች በማንኛውም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥረው እንዳይሰሩ መከልከሉ ይታወሳል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታሊባን የሴቶችን መብት ለማክበር የገባውን ቃል አለመፈጸሙን ተቃውሟል።
አፍጋኒስታናውያን ሴቶች ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያከናውናቸው ስራዎች ተቀጥረው እንዳይሰሩ መከልከሉንም ነው ተመድ ያስታወቀው።
በተለይ በናንግሃር ግዛት ክልከላው መጠናከሩን የሚያነሱት የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈር ዱጃሪክ፥ በመላ አፍጋኒስታን ሴቶችን መቅጠር አትችሉም ተብለናል ብለዋል።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በሴቶች ላይ የተጣለውን የስራ እገዳ በጽኑ መቃወማቸውን ነው አሶሼትድ ፕረስ የዘገበው።
በአፍጋኒስታን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ልዩ መልዕክተኛ ሪቻርድ ቤኔት በበኩላቸው፥ ታሊባን በሴቶች ላይ የሚፈጽመውን የመብት ጥሰት ሊያቆም እንደሚገባው አሳስበዋል።
ታሊባን ግን ስለሴት ሰራተኞቹ እገዳ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።
የመንግስታቱ ድርጅት በአፍጋኒስታን ካሉት 3 ሺህ 900 ሰራተኞች ውስጥ 600 ያህሉ አፍጋኒስታናውያን ሴቶች ናቸው።
ከአሜሪካ እና ኔቶ መራሹ ጦር የሁለት አስርት አመት ጦርነት በኋላ ዳግም ወደ ስልጣኑ የተመለሰው ታሊባን የሴቶችን መብት ለማክበር እንደሚሰራ ቢገልጽም ቃሉን መፈጸም አልቻለም ነው የተባለው።
ሴቶች በአፍጋኒስታን ከስድስተኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ የከለከለው የታሊባን መንግስት፥ በአለም አቀፍም ሆነ ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥረው እንዳይሰሩ አግዷል።
ታሊባን ሴቶችን ከትምህርት እና ስራ ማገዱ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያስከትልበትም ጊዜያዊ ነው ከሚል ማዘናጊያ መግለጫው ውጭ አቋሙን የማለዘብ ነገር አለማሳየቱን ነው የተነገረው።