ፈረንሳይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ አባያ መልበስ አገደች
በአዲሱ የትምህርት ዘመን በሙስሊም ሴቶች የሚለበሰው አባያ በመንግስት ትምህርት ቤቶች መከልከሉን አስታውቃለች
ፈረንሳይ በመንግስት ትምህርት ቤቶችና በመንግስት ህንጻዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን የሚከለክል ጥብቅ ህግ አላት
ፈረንሳይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሙስሊም ሴቶች የሚለብሱት አባያን መልበስ እንደምትከለክል የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
አባያ መልበስን የሚከለክለው አዲሱ ህግ በፈረንጆቹ መስከረም 4 2023 ከሚጀምረው አዲሱ የትምህርት ዘመን አንስቶ እንደሚተገብርም ተገልጿል።
ፈረንሳይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች እና በመንግስት ህንጻዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን መልበስም ይሁን መሳየት በጥብቅ የተከለከለ ነው።
በሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ በመንግስት በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጭንቅላትን እና ፊትን የሚሸፍኑ ሻርፖችና ስካርፎችን መከልከሏ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ አባያ የተባለውን የሴት ሙስሊሞችን ልብስ የከለከለች ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያም የፈረንሳይ ትምህርት ሚኒስቴር ጋብሪዬል አታል አስተያየት ሰጥተዋል።
የትምህርተ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት “አባያኃይምኖታዊ ምልክት ነው፤ ወደ ትምህርት ክፍል ስትገባ ተማሪዎችን በሚለብሱት ልብስ ኃማኖታቸውን መለየት የለብህም” ብለዋል።
በዚህም “ከዚህ በኋላ አባያ በፈረንሳይ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳይለበስ ውሳኔ አሳልፍያለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
በፈረንሳይ አባያን በትምህርት ቤቶች የመከልከል ውሳኔ ላይ የተደረሰው ለወራት ክርክር ከተደረገበት በኋላ እንደሆነም ተነግሯል።
ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 2024 ጭንቅላትን እና ፊትን የሚሸፍኑ ሻርፖችና ስካርፎችን፤ በ2010 ደግሞ ሙሉ ፊት የሚሸፍኑ ሂጃቦን መልበስን በይፋ መከልከሏ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም በሚሊየን የሚቆጠሩ ፈረሳውያን ሙስሊሞችን አስቆጥቷል።