የ ሲኤንኤን የ 2019 ጀግና ፍሬወይኒ መብራህቱ ማን ነች?
ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ የ 2019 የ ሲኤንኤን ጀግና በሚል የክብር ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ ለሽልማት ያበቃት ደግሞ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ሞዴስ ለታዳጊ ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች እና ሴቶች በሀገር ውስጥ አምርታ ማቅረቧ ነው፡፡
የ54 ዓመቷ ፍሬወይኒ በአሜሪካ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት የተከታተለች ሲሆን፣ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ 2005 ጀምሮ ታጥቦ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ታዳሽ ሞዴስ እያመረተች የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ችግር ማቃለል ችላለች፡፡ በተለይም ሴት ተማሪዎች ከወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ችግር ጋር በተያያዘ ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ማድረጓን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የተዛቡ ባህላዊ አመለካከቶች እንዲቀየሩም ፍሬወይኒ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ለሴት ተማሪዎች ስለ ወር አበባ ግንዛቤ በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተችም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ይህ መልካም ተግባሯ ነው ወ/ሮ ፍሬወይኒ ከ ሲኤንኤን የ2019 አስር የመጨረሻ ጀግኖች መካከል ከህዝብ በተሰበሰበ ድምጽ በቀዳሚነት እንድትመረጥ ያስቻላት፡፡ በዚህም ለአስሩ ጀግኖች ለእያንዳንዳቸው ከተበረከተው የ10 ሺ ዶላር በተጨማሪ፣ ወ/ሮ ፍሬወይኒ የ100 ሺ ዶላር ሽልማት አሸንፋለች፡፡
ትናንት ህዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. እሁድ ምሽት የክብር ሽልማቷን በተረከበችበት ወቅት “ምን እንደምል እንኳን አላውቅም፡፡ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል፤ ይህ ሽልማት የመላው ሴቶች ነው፡፡” ስትል ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ በዝግጅቱ ታዳሚያን ፊት ተናግራለች፡፡
ሽልማቱ ሲ.ኤን.ኤን. አለምን የተሸለ ስፍራ ለማድረግ ለሚተጉ ግለሰቦች በየአመቱ የሚያበረክተው ነው፡፡
ወ/ሮ ፍሩወይኒ ከስራ አጋሮቿ ጋር በመሆን ‘ማሪያም ሰባ’ በመባል በሚታወቀው የንጽህና መጠበቂያ ማምረቻ ፋብሪካዋ በየአመቱ 750,000 ሞዴሶችን ታመርታለች፡፡
እንደአውሮፓውያኑ ከ2009 ወዲህ 800,000 ያክል ልጃገረዶች እና ሌሎች ሴቶች የምርቷ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከከባቢ ጋር ተስማሚ እንደሆነ የተነገረለት ምርቱ አንዴ ጥቅም ላይ ውሎ የሚጣል ሳይሆን በአግባቡ ከተጠቀሙት ለሁለት አመታት ያክል የሚያገለግል ነው፡፡
ከ80% በላይ የሚሆነውን የወ/ሮ ፍሩወይኒ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ገዝተው በነጻ ለተጠቃሚዎች ያከፋፍላሉ፡፡ ከነዚህ ድርጅቶች አንዱ የሆነውና በወ/ሮ ፍሩወይኒ ስራ የተደመመው ዲጂታል ፔሬድ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ እገዛ እያደረገላት በትብብር መስራት ጀምሯል፡፡ እስካሁንም ከ150000 በላይ ሞዴሶችን ከፋብሪካው በመግዛት ለልጃገረዶች በነጻ አከፋፍሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወይዘሮ ፍሬወይኒ ከአጋር ድርጅቶች እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለልጃገረዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም የሚሰጡ ሲሆን እስካሁን ከ 300000 በላይ ሴቶች የስልጠናው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የ13 ዓመት ታዳጊ በነበረችበት ወቅት የወር አበባ ማየቷን የምትገልጸው ወይዘሮ ፍሬወይኒ፣ እንደ አብዛኛው ኢትዮያውያን ልጃገረዶች በወቅቱ ክስተቱ የእርግማን ውጤት እንደሆነ፣ እድለ ቢስ ሴት የመሆኗ ምልክት፣ ከዚህም ባለፈ ‘በቃ ላገባ ነው’? በሚል የተደበላለቀ ስሜት እንዲሰማት አድርጓት እንደነበር ተናግራለች፡፡ የፈጠራዋ መነሻ ምክኒያትም ይሄው እንደሆነ ነው የገለጸችው፡፡
ከወር አበባ ክስተት ጋር በተያያዘ ትምህርትን በአግባቡ አለመከታተል እና ማቋረጥ በሰለጠነው ዓለም ለሚኖሩ ሴት ተማሪዎች የሚታሰብ ባይሆንም፣ እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ግን ከዋነኛ ችግሮች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ገጠራማ ስፍራዎች ግማሽ ያክሉ ሴቶች ከወር አበባ ክስተት እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር የግንዛቤ ክፍተት በትምህርት ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንደሚፈጠር ሲ.ኤን.ኤን በዘገባው አስፍሯል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን