ፍሬድሪክ ሜርዝ ቀጣዩ የጀርመን መራሄ መንግሥት?
የ69 ዓመቱ ሜርዝ የፊታችን የካቲት በሚካሄደው ምርጫ የሀገሪቱ መሪ ሆነው የመመረጥ እድላቸው ሰፊ ነው ተብሏል
በውህደት መንግስት መስርተው የጀርመን መራሄ መንግሥት የሆኑት ኦላፍ ሾልዝ ምርጫ እንዲደረግ ወስነዋል
ፍሬድሪክ ሜርዝ ቀጣዩ የጀርመን መራሄ መንግሥት?
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን የፊታችን የካቲት ላይ ምርጫ ታካሂዳለች።
በዚህ የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ላይ ከአራት በላይ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል።
የወግ አጥባቂው ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ዩኒየን ፓርቲ መሪ የሆኑት ፍሬድሪክ ሜርዝ በዚህ ምርጫ ላይ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ሰፊ ግምት እንዳላቸው ዶቸ ቪሌ ዘግቧል።
የቀድሞ መራሂት መንግሥት አንጌላ መርክል ተቀናቃኝ የነበሩ ሜርዝ በአብዛኛው ጀርመናዊያን ተወዳጅ ናቸውም ተብሏል።
የ69 ዓመቱ ሜርዝ ምርጫውን ካሸነፉ በእድሜ ከገፉ የጀርመን መሪዎች መካከል ሁለተኛው ሰው ይሆናሉ።
የካቶሊክ ዕምነት ተከታይ እና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት ሜርዝ ከወቅቱ የጀርመን መራሄ መንግሥት የተሻለ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ተገምቷል።
የነዳጅ ፍላጎቷን ከሩሲያ ትሸምት የነበረችው ጀርመን ከዩክሬን ጦርነት በኋላ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ አለመረጋጋት አጋጥሟታል።
ለዩክሬን የሚሰጥ ድጋፍ፣ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ እንደ ቮልስዋገን እና መሰል የጀርመን ግዙግ ኩባንያዎች የትርፍ ማሽቆልቆል ጉዳይ ጀርመናዊያንን እያሳሰቡ ካሉ ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳዎች ናቸው።