ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ የ50 አመት እድሜ ያለው የሳኡዲ አረብያ ዜጋ መሆኑ ታውቋል
በጀርመን ማግደቡርግ ከተማ የገና ገበያ ላይ በደረሰ የመኪና ጥቃት የሟቾች ቁጥር አራት መድረሱን የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
አንድ የሳኡዲ አረብያ ዜግነት ያለው ግለሰብ ህዝብ በተሰበሰበበት የገና ገበያ ውስጥ ጥሶ በመግባት ባደረሰው ጉዳት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር በፀጥታ እና በስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ክርክር እየተካሄደ በሚገኝበት የምርጫ ወቅት የተፈጠረው ጥቃት ለቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ሀሳብ መግነን በር ከፍቷል፡፡
ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ሁለት ሰዎች ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የገቡ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡
የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ እንደዘገበው 41 ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 86 ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው፤ ቀሪ 78 ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት አስተናግደዋል፡፡
የሀገሪቱ የጸጥታ ባለስልጣናት ከመኪና ጥቃቱ ጋር በተያያዘ በጀርመን ለሁለት አስርት አመታት የኖረውን የ50 አመት የሳዑዲ አረብያ ዜግነት ያለው ዶክተር ላይ ምርመራ እያከናወኑ ነው፡፡
ግለሰቡ ጥቃቱን በምን ምክንያት እንደፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ፖሊስ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት በግለሰቡ መኖርያ ቤት ላይ ፍተሻ አካሂዷል፡፡
ሮይተርስ ከሳኡዲ አረብያ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ግለሰቡ ጥቃቱን ከማድረሱ በፊት በግል ኤክስ (ትዊተር ) ገጹ ላይ “የጽንፈኛ” አመለካካት የሚያንጸባርቅ መልዕክት መለጠፉን ተከትሎ ለጀርመን ባለስልጣናት ሪያድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብላለች፡፡
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ በዛሬው ዕለት አደጋው በደረሰበት ስፍራ ጉብኝት ያደርጋሉ የሚጥበቅ ሲሆን፤ በአስቸኳይ ምርጫ መንግስታቸውን እያቀናቀነ የሚገኘው ኤኤፍዲ ፓርቲ በስደተኛ ፖሊሲዎች ዙርያ ጠንካራ ማሻሻያ እንዲደረግ እየጠየቀ ነው፡፡