ከብሪታኒያ እስከ አዘርባጃን፡ ፑቲን "ተደርገውብኝ ነበር" ካሏቸው አምስት የግድያ ሙከራዎች እንዴት ተረፉ?
ከዚያም ወዲህ ፑቲን በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ሁሉ እንቅስቃሴዎችን አነፍንፈው ለመለየት የሚችሉ ድንቅ ስናይፐር ተኳሾች ይከተሏቸዋል
ፑቲን ላይ ከተቃጡ የግድያ ሙከራዎች የቅርቡ ከወራት በፊት የተፈጸመ ነበር ተብሏል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን ከአምስት የግድያ ሙከራዎች መትረፋቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡
የእንግሊዙ ዘ ሰን ጋዜጣ የቅርቡ የግድያ ሙከራ የዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ሰሞን የተደረገ ነው ሲል ሙከራዎቹን የተመለከቱ ዘገባዎችን ይዞ ወጥቷል፡፡
ፑቲን ከሁለት ወራት በፊት በካውካሰስ አካባቢ በግለሰቦች የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበርም ፕራቫዳ ከተሰኘው የዩክሬን ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩክሬን ጦር የወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ ተናግረዋል፡፡
ከዚያም ወዲህ ፑቲን በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ሁሉ ሊያጋጥሙ የሚሉ የግድያ ሙከራዎችንና የአልሞ ተኳሾችን እንቅስቃሴ አነፍንፈው ለመለየት የሚችሉ ድንቅ ስናይፐር ተኳሾችን ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ነው የተነገረው፡፡
የስናይፐር ተኳሾቹ ዋና ስራ ፑቲን በሌሎች አልሞ ተኳሾች ዒላማ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት አልሞ ተኳሾች መኖር አለመኖራቸውን ማረጋገጥና አካባቢውን ከስጋት ነጻ ማድረግ ነው፡፡
"አምስት ጊዜ ሊገድሉኝ ሞክረዋል" - ፑቲን
እንደ ዘ ሰን ከሆነ ፑቲን ለግድያ የሚከታተሏቸው አካላት እንዳሉ በማሰብ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ወደ እርሳቸው ሊቀርቡና ሊያገኟቸው የሚችሉትን የጥበቃ ቡድን አባላቶቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ላለመመረዝ በሚል የሚመገቡትን ቀድሞ የሚቀምስ አካል አለ፡፡
ፑቲንን የመግደሉ ሙከራ ከፈረንጆቹ 2022 የጀመረ ነው እንደ ጋዜጣው ዘገባ፡፡ በወቅቱ ከአፍጋኒስታን ጋር ግንኙነት እንዳለው የተነገረለት አንድ ኢራቃዊ ዜጋ በአዘርባጃን ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመጠቀም በፑቲን ላይ የግድያ ሙከራን ለማድረግ ሲያሴር በመገኘቱ ከነ ግበረአበሮቹ ተይዞ አስር ዓመት ተፈርዶበታል፡፡
ሁለተኛው ሙከራም በዚያው ዓመት በፈረንጆቹ 2002 የተደረገ ነው፡፡ ይህ ግን በዚያው በሃገራቸው በሩሲያ በቤተመንግስታቸው በክሬሚሊን አቅራቢያ የሆነ ነው፡፡
በወቅቱ የፕሬዝዳንቱ ተሽከርካሪ በቤተመንግስቱ አቅራቢያ በሚገኝ አውራ ጎዳና እንደሚያልፍ ይጠበቅ ነበረ፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም በአውራ ጎዳናው አዳዲስ ባነሮችን ለመስቀል ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡
ሆኖም ከአንድ ሰዓት በኋላ ሽር ጉዱ በዝቶ በነበረበት ስፍራ ፑቲን ሲያልፉ እንዲፈነዳ ታስቦ የተዘጋጀና 40 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፈንጅ መገኘቱን አንድ የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛ ዘግቧል፡፡ ሁኔታውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱና አጃቢዎቻቸው መንገድ ቀይረው መጓዛቸውም ነው በጋዜጣው የተጠቀሰው፡፡
ሶስተኛው በፈረንጆቹ በ2003 በብሪታኒያ የተደረገ ነው፡፡ በወቅቱ የብሪታኒያ የጸረ ሽብር ፖሊስ ፑቲንን ለመግደል ተሸርቦ የነበረውን ሴራ ማክሸፉን አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ሰንደይ ታይምስ ግድያውን ሊፈጽሙ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ያለምንም ክስ መለቀቃቸውን ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ አንደኛው ተጠርጣሪ የሩሲያ የስለላ ተቋም (ኬ.ጂ.ቢ) የቀድሞ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፡፡
አራተኛው በሩሲያ ላይ አምጸው ከነበሩ የቸቸን (ቺቺኒያ) አማጽያን መካከል አንዱ በሆነውና አዳም ዑስማየቭ በተባለ ግለሰብ ሊፈጸም የነበረ ነው፡፡ ሆኖም የዩክሬን ልዩ ኃይሎች ውጥኑን ደርሰውበት ዑስማየቭን ኦዴሳ በተባለችው የወደብ ከተማ በቁጥጥር ስር አውለውታል፡፡
ግለሰቡ በወቅቱ ሊፈጽመው ከነበረ ግድያ ጋር በተያያዘ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ቃሉን የሰጠ ሲሆን ወደ ሞስኮ አቅንቶ ፑቲንን ለመግደል ሲያሴር እንደነበር ተናግሯል፡፡
የኋላ ኋላ የሩሲያ የደህንነት ተቋማት እንዳሳወቁት ከሆነ ዑስማየቭ ከዝነኛ የብሪታኒያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀና ፑቲንን አጥብቀው በመቃወም ከሚታወቁ የቸቸን ቤተሰቦች የተገኘ ነው፡፡
አምስተኛው እና የቅርብ ነው የተባለው ደግሞ ቀደም ሲል በዘገባው መግቢያ እንደተጠቀሰው የዩክሬን ጦርነት በተጀመረ ሰሞን ከሶስት ወራት በፊት የተደረገ ነው፡፡ ሙከራው መደረጉንም የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ኪሪል ቡዳኖቭ ናቸው የተናገሩት፡፡
ኃላፊው ለኡክራኒስካ ፕራቭዳ እንደገለጹት ከሆነ ሩሲያ ባሳለፍነው የካቲት 24 በዩክሬን ላይ ልዩ ዘመቻን ባወጀች ሰሞን ፑቲንን የመግደል ያልተሳካ ሙከራ በካውካሰስ አካባቢ ተደርጓል፡፡
ካውካሰስ (ካውኬዢያ) የሚባለው አካባቢ በጥቁር ባህር እና በካስፒያን ባህር መካከል የሚገኙትን አርመንን፣ አዘርባጃንን፣ ጆርጂያንና በደቡባዊ ሩሲያ የሚገኙ ሌሎች አካባቢዎችን ያካትታል፡፡
ሆኖም የቅርብ ነው የተባለውንና ያልተሳካውን ፕሬዝዳንት ፑቲንን የመግደል ሙከራ በተመለከተ ከሩሲያ በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡ ሞስኮው እንዲህ ዐይነቱ መረጃ የስነ ልቦናዊ ጦርነቱ አካል ሆኖ ከዩክሬን በኩል የሚነዛ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ግን ደጋግማ ገልጻለች፡፡