ፖለቲካ
ጦርነቱ ሊቋጭ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ከፑቲን ጋር መገናኘት ነው - የዩክሬን ፕሬዝዳንት
በሩሲያ ላይ የተጀመሩት ማዕቀቦች እና እገዳዎች ጠንከር ብለው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል
ዘለንስኪ ስለ ጦርነቱ ማብቃት የምናወራ ከሆነ ያለ ፑቲን የሚሆን አይደለም ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጦርነቱን ለመቋጨት ብቸኛው መንገድ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ማግኘት እንደሆነ ተናገሩ፡፡
ዘለንስኪ ፑቲንን በግንባር አግኝቶ ማውራቱ ጦርነቱን ለማቆም ብቸኛው መንገድ ነው ብለዋል፡፡
በሩሲያ ሁሉ ነገር የሚወሰነው በፕሬዝዳንቱ ነው ያሉት ዘለንስኪ ስለ ጦርነቱ ማብቃት የምናወራ ከሆነ ያለ ፑቲን የሚሆን አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይሄን ያሉት ትናንት ሰኞ ፤ በስዊዘርላንድ ዴቮስ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ነው፡፡
ማሪዎፖል የተባለችውን የወደብ ከተማ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሯን ያስታወቀችው ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን የጀመረችውን ዘመቻ አጠናክራ መቀጠሏን አስታውቃለች፡፡
ዘመቻው በአካባቢው የሚገኙትን የዶንባስ አካባቢዎች ነጻ በማውጣት ሪፐብሊክ ሆነው እንዲመሰረቱ ለማድረግ ነው፡፡ የሩሲያ ጦር ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ የሉሃንስክ ሪፐብሊክን እውን ለማድረግ ጥቂት ብቻ ይቀረናል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ዜሌንስኪ በፎረሙ ባደረጉት ንግግር በሩሲያ ላይ የተጀመሩት ማዕቀቦች እና እገዳዎች ጠንከር ብለው እንዲቀጥሉ ስለመጠየቃቸውም ዘ ናሽናል ዘግቧል፡፡