እፎይታው እስከ ዓመቱ መጨረሻ ይዘልቃል
የቡድን 20 አባል ሃገራት ለደሃ ሃገራት የብድር እፎይታ ለመስጠት ተስማሙ
የዘንድሮውን አመታዊ ኮንፈረንስ በሳዑዲ አረቢያ አስተናጋጅነት በኦን ላይን ቪዲዮ ያካሄዱት የቡድን 20 አባል ሃገራት የደሃ ሃገራትን የእዳ ጫና በማቅለል እፎይታ እንዲያገኙ ለማድረግ ወስነዋል፡፡
ውሳኔው ብድሩንና ወለዱን ጨምሮ ይከፈል የነበረውን እስከ 20 ቢሊዬን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ሃገራት የጤና ስርዓታቸውን ለማሻሻልና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያውሉት ለማድረግ እንደሚያስችል የሳዑዲ የፋይናንስ ሚኒስትር ሞሃመድ አል ጄዳን ተናግረዋል፡፡
እፎይታው እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 መጨረሻ ድረስ የሚዘልቅ ነው እንደ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ፡፡
የአባል ሃገራቱ የዘንድሮው ኮንፍረንስ የፋይናንስ ሚኒስትሮችንና የበሄራዊ ባንክ ገዢዎችን ለ2 ያህል ሰዓታት ያገናኘ ነው፡፡
ኮንፍረንሱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ለዓለም የጤና ድርጅት የምታደርገውን ድጋፍ ማቋረጣቸው ከቡድኑ አባል ሃገራት ጭምር ሳይቀር ክፉኛ እያስተቻቸው ባለበት ወቅት የተካሄደ ነው፡፡
የብድር እፎይታው በዓለም ባንክ እና በመንግስታቱ ድርጅት መስፈርተኞች ተመዝነው ድሃ እና ያላደጉ ለተሰኙ እንዲሁም ብድር በመመክፈል ላይ ያሉ ሃገራትን የሚመለከት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ ብሉምበርግ በተሰኘ ዓለም አቀፍ የዜና ተቋም የኦንላይ ህትመት ውጤት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ዓለም አቀፉ አበዳሪ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) የአፍሪካን የብድር ጫና እንዲያቀል መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
የቡድኑን እርምጃ የግል አበዳሪ ተቋማት ጭምር ደግፈውታል፡፡