የካቲት አጋማሽ የጀመረ ነው በተባለው ጥቃት 5 ሰዎች ሲጎዱ የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል
በባምባሲ የአንበሳ ጥቃት ተባብሷል
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ በአንበሶች የሚደርሰው ጥቃት እየተበራከ መምጣቱ ተሰምቷል፡፡
ብዙዎችን ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች የዳረገው ጥቃቱ የ3 ሰዎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመንጠቁም ነው የተነገረው፡፡
ቃላቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ/ም ጀመረ ነው ይላሉ፡፡ ከዛን ቀን ወዲህ የወረዳውን የተለያዩ ቀበሌዎች እያዳረሰና እየተበራከተ መምጣቱን በመግለጽ፡፡ በተጠቀሰው ዕለት መንደር 47 ተብሎ በሚጠራ የወረዳው አካባቢ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል፡፡
ከዛን ቀን ወዲህ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተዛመተ የመጣው ጥቃት ለጋወርቄ ወይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጉልማ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ደርሶ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ/ም አንድ የ19 አመት ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል፡፡
ዛሬ ሌሊቱን ደግሞ (ሚያዚያ 6 ቀን 2012 ዓ/ም ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ) ሸቦራ በሚባል ቀበሌ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቱን አጥቷል፡፡
ግለሰቡ ለእርሻ ስራ ተሰምርቶ ከነበረበት አካባቢ ተመልሶ በቤቱ ውስጥ እግሩን እየታጠበ ሳለ ነው ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በድንገት ወደ ቤቱ በገባው አንበሳ ጥቃት የደረሰበት፡፡በአንገቱ እና በሌላው የሰውነት ክፍሉ ላይ በደረሰበት ጥቃትም ህይወቱ ወዲያውኑ ሊያልፍ ችሏል፡፡
አስከሬኑ አማራ ክልል ወደሚገኙ ቤተሰቦቹ መላኩንም ነው መረጃውን ያደረሰን የወረዳው መንግስት ኮሙኒኬሽን ለአል ዐይን የገለጸው፡፡
ከአሁን ቀደምም በአካባቢው ተመሳሳይ ጥቃቶች ደርሰዋል፡፡ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች እዚያው ባምባሲ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ታክመው መዳናቸውና ከፍ ያለ ጉዳት ያለባቸው ወደ አሰሶ ለተጨማሪ ህክምና መላካቸውም ተሰምቷል፡፡
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኦፊሠር ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው ተረፈ “ጥቃቱ በወረዳው 5 የገጠር ቀበሌዎች በሠው እና በእንስሳት የደረሰ ነው” ብለዋል።
አንበሳው 10 ሺህ ብር በሚገመቱ የቤት እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ስለመናገራቸውም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡
የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ያሲር አብዱልመጅድን ዋቢ ያደረገው የኢዜአ ዘገባ ደግሞ ጥቃቱ ኮልማ እና ሽንግላ በተሰኙ የወረዳው ቀበሌዎች በአንዲት አንበሳ መድረሱን ያትታል።
በኮልማ ቀበሌ ከሶስት ቀናት በፊት በእርሻ ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሁለት ሰዎችን አሳድዳ በማጥቃት ህይወታቸው ማለፉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
ትናንት ምሽት በአንድ ግለሰብ ላይ የደረሰው ጥቃት ደግሞ በሽንግላ ቀበሌ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የጥቃት አድራሿ አንበሳ ልጇ(ደቦል) በሰዎች ተይዞ መሸጡን የሚገልጽ መረጃ ፖሊስ እንደደረሰው ያመለከቱት ምክትል ኢንስፔክተሩ በዚህም ተቆጥታ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
የአንበሳዋ ደቦል የሚገኝበትን አድራሻ ለማፈላግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
ፖሊስ አንበሳዋ በህብረተሰቡ ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳታደርስ ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ጥቃቱ በተፈጸመበት እና አጎራባች ቀበሌዎች የሚገኙ የህብረሰተብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
ስለ ጥቃቱ መደጋገም ያስታወሱ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም
“በተለይ በበረሀ ውስጥ በእርሻ ስራ ላይ የተሠማራችሁ በከብት ጥበቃ ፣ ለማር ቆረጣ ፣ እንጨት ለማምጣት እና ለተለያዩ ስራ ወደ በረሀ የምትሄዱ ጥንቃቄ አድርጉ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።