የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ ቦታ ለሱዳን ተመልሶ ተሰጥቷል በሚል የወጣው ዘገባ ውሸት ነው ተባለ
ለሱዳን ተመልሶ የተሰጠ ቦታ የለም
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ ቦታ ለሱዳን ተመልሶ ተሰጥቷል በሚል የወጣው ዘገባ ውሸት መሆኑ ተገለጸ።
አል ፋሽቃ የሚባል ቦታ ለሱዳን ተመልሷል እየተባለ ቢወራም ከሰሞኑ ሁለቱ ጎረቤት ሃገሮች በድንበር ጉዳይ ያደረጉት ስምምነት የለም ነው የተባለው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ለአል አይን ኒውስ እንዳስታወቁት አንዳንድ ሚዲያዎች ስለጉዳዩ ቢዘግቡም ጉዳዩ ግን ውሸት ነው ።
አሽራቅ አል አውሳት የተባለውና መቀመጫውን እንግሊዝ ለንደን ያደረገው የአረቡ ዓለም ጋዜጣ ኢትዮጵያና ሱዳን ለዓመታት “ይወዛገቡበታል” ያለውን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት አል ፋሽቃ የተሰኘው ግዛት ተመልሶ ለሱዳን እንዲሰጥ ተስማምተዋል በሚል መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ዘገባ ላይ ጠንከር አስተያየትን ሰጥተዋል፡፡
የ“ቁሞ ቀር ፖለቲኞችና የውጭ ቅጥረኛ ሚዲያዎች” ቁማር ነው በሚል እንዲታለፍም ነው በትዊተር የማህበራዊ ገጻቸው የጠየቁት፡፡
ያሳለፍነው አርብ ወደ ካርቱም ያቀኑት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውም አይዘነጋም፡፡