እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ ተጠባቂ ሀገራት መሪዎች እንደማይገኙ በተገለጸበት በዚህ ጉባኤ ላይ አዳዲስ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑበት ይጠበቃል
በዘንድሮው የቡድን 20 ሀገራት ዋና ዋና አጀንዳዎች ምን ምን ናቸው?
ባላቸው ኢኮኖሚ አቅም ከአንደኛ እሰከ 20ኛ ደረጃ ድረስ ያሉ የዓለማችን ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ነው የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ፡፡
ጉባኤው በቡድኑ አባል ሀገራት በየጊዜው እየተዘዋወረ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮውን ጉባኤ አዘጋጅ ሀገር ሩቅ ምስራቋ ሕንድ ነች፡፡
በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ መሪዎች ወደ ስፍራው መጓዝ የጀመሩ ሲሆን የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ እና የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን እንደማይገኙ አስቀድመው ተናግረዋል፡፡
ኒው ደልሂ የቡድን 20 ጉባኤ በዝንጀሮዎች እንዳይረበሽ እየተዘጋጀች ነው
ጉባኤው አንድ ምድር-አንድ ቤተሰብ- አንድ ግብ በሚል መሪ ሀሳብ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል ተብሏል፡፡
ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ጉዳይ፣ በጸጥታ ጉዳይ፣ የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ ስጋቶች እና እድሎች የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ዋነኛ መወያያ አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን በተለይም ጉዳቱን እንዴት መቀነስ ይቻላል፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ሀገራት እንዴት መደገፍ ይቻላል እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሀይል አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ ውይይቶች እና አዳዲስ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም የቡድን 20 ሀገራት ለዓለም አለመረጋጋት ምክንያት የሆኑት የጸጥታ ስጋቶች፣ የአፍሪካ መፈንቅለ መንግስት ግልበጣ፣ ድህነት፣ ሰብዓዊ መብት ስጋቶች እና የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ሌላኛው ተጠባቂ መወያያ አጀንዳዎች ናቸው፡፡