ፕሬዝዳንት ባይደን 21 አሜሪካውያን ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ መሸለማቸውን አስታውቀዋል
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ የአሜሪካን ብሄራዊ የሳይንስ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ተበረከተላቸው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን 21 አሜሪካውያን በዛሬው እለት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፎች ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ መሸለማቸውን አስታውቀዋል።
ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ከተሸለሙት መካከል ትውለድ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ እንደሚገኙበትም ባይደን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ዝርዝር ላይ አመላክተዋል።
በዚህም ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ በሳይንስ ዘርፍ የአሜሪካ ብሔራዊ የክብር ሜዳሊያ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እጅ ተበርክቶላቸዋል።
መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጋቢሳ ኤጄታ ለሽልማቱ ያበቃቸው በከፍተኛ የምርምር ስራቸው የእፅዋት ዘረመል ምህንድስና በመጠቀም በረሃማ የአየር ንብረት እና ነፍሳትን የሚቋቋሙ የአዝርዕት ዘሮችን በማግኘታቸው ነው።
ፕሮፌሰር ገቢሳ በተለያየ ጊዜ በማሽላ ላይ ባገኙት አስደናቂ ምርምር የተለያዩ ድቅል የሆኑ የማሽላ ዘሮችን መፍጠር የቻሉ ከ200 በላይ የምርምር መጽሃፍቶችን አሳትመዋል።
ከ17 በላይ ታላላቅ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) 2009 የዎርድ ፉድ ፕራየዝ ተሸላሚም መሆናቸውም ይታወሳል።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ ከዚህ ቀደምም ጥገኛ አረምን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ለማዳቀል ለሚሰሩት ምርምር ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ግብረ-ሰናይ ድርጅት አምስት ሚሊዮን ዶላር ማሸነፋቸውም አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ በአሜሪካው የፑርድ ዩኒቨርሲቲ ሥመ-ጥር ተመራማሪ ለመሆን በቅተዋል።
ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ላደረጉት እገዛ ከበሬታ የተቸራቸው ተመራማሪ ናቸው።