ለእስራኤልና ለዩክሬን የሚደረጉ ወታደራዊ ድጋፎች እንደሚጠናከሩ ባይደን አስታውቀዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእስራኤል ጉብኝታቸው ከተመለሱ በኋላ በትናንትናው እለት ምሽት በነጩ ቤተ መግስት ንግግር አድርገዋል።
ባይደን በንግግራቸውም ስለ እስራኤልና ሃማስ ጦርነት እንዲሁም ስለ ዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ያነሱ ሲሆን፤ የአሜሪካ ኮንግረስ ለሁለቱም ሀገራት የደጋፍ ማእቀፎች ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍም ጠይቀዋል።
ባይደን ለእስራኤልና ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ምን ያክል እንደሚያስፈልጋቸው በይፋ ባይናገሩም፤ 100 ቢሊየን ዶላር ሊጠይቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለ ዩክሬን እና እስራኤል ጦርነት ባደረጉት ንግግራቸውም የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሃማስን አነጻጽረዋል።
"ሃማስ እና ፑቲን የተለያዩ ስጋቶችን ደቅነዋል” ያሉት ባይደን “ነገር ግን ሁለቱም የጎረቤት ሀገር ዲሞክራሲን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት መፈለጋቸው ያመሳስላቸዋል” ብለዋል።
" የፑቲንን የስልጣን ጥማትና እና የዩክሬን የመቆጣጠር ፍላጎት ካላቆምን በዩክሬን ብቻ አይወሰንም" ሲሉም ተናግረዋል።
ባይደን አክለውም፤ ሃማስ “በዓለም ላይ የክፋትን ጥግ ያሳየን ሰይጣናዊ ተግባር ፈጽሟል፤ ለእኔ ከታገቱት አሜሪካውያን ደህንነት የበለጠ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ የለኝም” ሲሉ አሳስበዋል።
"እስራኤል እና ዩክሬን ስኬታማ መሆናቸውን ማረጋገጥ ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ወሳኝ ነው" በማለትም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
አሸባሪዎች እና አምባገነኖች ዋጋ መክፈል አለባቸው ሲሉም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በንግግራቸው አስታውቃል።