ፕሬዝዳንት ባይደን ሪፐብሊካኖች የዩክሬንን እርዳታ ውድቅ በማድረጋቸው ጫና እያደረጉባቸው ነው
በሀገሪቱ ህግ አውጭዎች የጸደቀው ጊዜያዊ በጀት የኪየቭን ድጋፍ አላካተተም
ዋሽንግተን የኪየቭ ከፍተኛ ድጋፍ አቅራቢ ሀገር ናት
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሪፐብሊካን የሆኑ የሀገሪቱ ህግ አውጭ ም/ቤት አባላት ለዩክሬን ተጨማሪ እርዳታን የሚፈቅድ አዋጅን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ የመንግስት ተቋማትን ለመከርቸም ጫፍ ላይ የነበረውን የፖለቲካ ማውጣት ማውረድ "ሰልችቶኛል" ሲሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ም/ቤቱ አራት ሚሊዮን የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ እንዳይቋረጥና መንግስት እንዳይዘጋ ያደረገ የሦስት ወራት በጀት መድቧል።
በጀቱ በዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፤ ለኪየቭ ድጋፍ ግን አላካተተም።
ዋሽንግተን የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ባለፈው ዓመት ከተጀመረ ወዲህ የኪየቭ ከፍተኛ ድጋፍ አቅራቢ ናት።
ፕሬዝዳንት ባይደን የሀገራቸውን ጨምሮ ዩክሬን የዓለም ድጋፍ እንዳይሳናት ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሪፐብሊካኖች ለዩክሬን ድጋፍ ሌላ ድምጽ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል በማለት ድጋፉ እንዲጸድቅ ጫና እያደረጉ ነው ተብሏል።
"በምንም አይነት ሁኔታ የአሜሪካ ድጋፍ ለዩክሬን መቋረጥ የለበትም። አፈ ጉባኤው የገቡትን ቃልና ዩክሬን ራሷን ከጥቃት እንድትከላከል ድጋፍ ለማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ በሙሉ እምነት እጠብቃለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በቅርቡ ዋሽንግተንን ለጎበኙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ምንም እንኳ ከሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ለኪየቭ እርዳታቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።