የ180 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የጥንቆላ ግድያ
በሄይቲ ልጁ የታመመበት የወንበዴዎች መሪ በጠንቋዮች ምክር በእርጅና እድሜ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን ገድሏል

የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መንሰራፋት ራስምታት በሆነባት ሀገር በ2024 ብቻ ከ5 ሺህ በላይ ንጹሀን ተገድለዋል
በሄይቲ ጠንቋይ ናቸው በተባሉ አረጋውያን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት 180 የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡
በወንበዴዎች እየታመሰች በምትገኘው የካርብያን ሀገር ሄይቲ የተደራጁ የወንጀል ቡድን መሪዎች በንጹሀን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም፡፡
ዋርፍ ጄርሚ የተባለው የወሮበላ ቡድን መሪ የሆነው ሞኔል ሚካኖ ፌሊክስ የልጁን መታመም ተከትሎ በዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ ውስጥ በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት በሲቲ ሶሌይል መንደር የሚገኙ አረጋውያን እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አረጋውያኑ እንዲገደሉ ትዕዛዝ የተሰጠው በመንደሩ የሚኖሩ አዛውንቶቹ የወሮበሎች ቡድን መሪው ልጅ እንዲታመም የጥንቆላ ተግባር መፈጸማቸውን ከጠንቋዮች የተቀበለውን ምክር ተከትሎ ነው፡፡
የሀገሪቱ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ኔትዎርክ ይፋ ባደረገው መረጃ አርብ ዕለት ቢያንስ 60 ሰዎች ቅዳሜ ደግሞ 50 ሰዎች በገጀራ እና ቢላዋ በተፈፀሙ ጥቃቶች የተገደሉ ሲሆን ሁሉም ተጎጂዎች ከ60 ዓመት በላይ የሚሆናቸው ናቸው ብሏል፡፡
በጥንቆላ ታሟል የተባለው የውሮበላ ቡድኑ መሪ የመጨረሻ ልጅ ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ህይወቱ አልፏል፡፡
የጥቃቱ ኢላማ ከተደረጉ አዛውንቶች በተጨማሪ ነዋሪዎችን ለመከላከል ጣልቃ የገቡ የአካባቢው ወጣቶችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
ከሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መግለጫ እስከ ትላንት ድረስ በአጠቃላይ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 180 መጠጋቱን አስታውቋል፡፡
መግለጫው አክሎም ቀይ መስመር ተጥሷል፤ የዋርፍ ጄርሚ የወሮበላ ቡድን መሪ ሞኔል ሚካኖ ፌሊክስን ጨምሮ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ተከታትሎ ለማጥፋት መንግስት ግብረ ሀይል ያቋቁማል ነው ያለው፡፡
በአለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ፖሊሶች ጥረት ጭምር መገታት ያልቻለው የሄይቲ የወሮበላ ቡድኖች የወንጀል እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ይገኛል፡፡
በ2024 ብቻ ከአምስት ሺህ በላይ ንጹሀን በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መገደላቸውን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ የሚገኝው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
በፖለቲካዊ ሽኩቻ የተወጠረው መንግስት በመዲናዋ እና በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣውን የወንበዴዎች ሃይል ለመቆጣጠር በመታገል ላይ ይገኛል፡፡
የታጠቁት ቡድኖች በዘፈቀደ ግድያ፣ የቡድን አስገድዶ መድፈር፣ በእገታ እና አሳሳቢ የሆነውን የምግብ እጥረት በማባባስ ይከሰሳሉ፡፡