ኔታንያሁ በቀረበባቸው የሙስና ክስ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሱን ፖለቲካዊ አለማ ያለውና መሰረተ ቢስ ነው በሚል አጣጥለውታል

በኔታንያሁ የክስ መዝገብ ለመመስከር 140 የሚጠጉ ሰዎች እንደሚቀርቡ ተነግሯል
በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የቀረበው የሙስና ወንጀል ክስ መታየት ጀመረ።
በቴል አቪቭ ወደሚገኘው ፍርድቤት በዛሬው እለት ያቀኑት ኔታንያሁ በ2019 ነበር ጉቦ በመቀበል፣ በማጭበርበር እና ህዝብ የጣለባቸውን እምነት በማጉደል ሶስት ክሶች የቀረቡባቸው። ይሁን እንጂ ክሱ በጋዛው ጦርነት ምክንያት ሳይታይ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፍርድቤት ሲያመሩ ከ100 በላይ የሚሆኑ በጋዛ ታግተው የሚገኙ ዜጎች ይለቀቁ የሚሉ ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ኔታንያሁ በጋዛው ጦርነት ክሳቸው መታየቱ እንዲዘገይ አድርገው የቆዩ ቢሆንም ባለፈው ሀሙስ ዳኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድቤት ቀርበው ክሱ መታየት እንዲጀምር መወሰናቸውን ሲኤንኤን አስታውሷል።
በዚህም የጋዛው ጦርነት ባልተቋጨበትና በሶሪያ የበሽር አልአሳድ አገዛዝ ተወግዶ እስራኤል ጦሯን ባስጠጋችበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳምንት ሶስት ጊዜ ፍርድቤት ይመላለሳሉ።
በሶስት የተለያየ ጊዜ ከሚሊየነር ጓደኞቻቸው ህጋዊ ባልሆነና እነርሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ስጦታ ተቀብለዋል፤ አፍቅሮተ ሚዲያቸውን ለማሳካትም ከመገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች ጋር ያልተገባ ሽርክና ፈጥረዋል የሚል ክስ በቀረበባቸው ኔታንያሁ ላይ 140 የሚጠጉ ስክሮች እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
ከምስክሮቹ ውስጥም የኔታንያሁ የቅርብ ወዳጅ የነበሩና ፊታቸውን ያዙሩባቸው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያር ላፒድ፣ የቀድሞ የደህንነት ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች ይገኙበታል ተብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የድምጽ ቅጂዎች፣ የፖሊሲ ሰነዶች እና የጽሁፍ መልዕክት ልውውጦች በክርክር ሂደቱ ላይ እንደሚቀርቡም ነው የተነገረው።
ከሶስት ወራት በኋላ ትናንት ምሽት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ኔታንያሁ፥ በቀረበባቸው ክስ ዙሪያ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ "እውነታውን ለማስረዳት ይህቺን ቀን ለስምንት አመታት ስጠብቃት ነበር" ብለዋል።
በሀሰተኛ ዜናዎች ስማቸውን ለማጠልሸት የሚፈልጉ ፖለቲካዊ ሻጥር ላይ የተሰማሩ አካላት ክሱን እንዳቀነባበሩትም ነው ያነሱት።
"በእስራኤል ዴሞክራሲ ትክክለኛውን አደጋ የደቀኑት በህዝብ የተመረጡት አይደሉም፤ የህዝብን ድምጽ ማክበር የማይፈልጉ የህግ አስፈጻሚ አካላት እንጂ፤ እነዚህ አካላት በፈጣን ፖለቲካዊ ምርመራ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ የሚፈልጉ ናቸው" ሲሉም ክሱን አጣጥለዋል።
ህግ አስፈጻሚ አካላት ምስክሮችን የመረመሩበትን መንገድም መቃወማቸውን ሲኤንኤን አስነብቧል።
በኔታንያሁ ላይ የሚቀርቡ የሙስና ክሶች እስራኤላውያንን ለሁለት ከፍለው አምስት ዙር የዘለቀ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው አመት የዳኞችን ስልጣን ለመገደብ መሞከራቸውም ተቃውሞ እንዳስነሳባቸው አይዘነጋም።
እስራኤልን ከ2009 ጀምሮ ለተከታታይ በሚባል ደረጃ የመሩት የ75 አመቱ ቤንያሚን ኔታንያሁ በስልጣን ላይ እያሉ በወንጀል ክስ ፍርድቤት የቀረቡ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤትም ባለፈው ወር በጋዛ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የእስር ማዘዣ እንዳወጣባቸው የሚታወስ ነው።